የአንጎላ የውጭ መረጃ አገልግሎት እና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በደኅንነትና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመሥራት እና የነበሩ ትብብሮችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ የሚያስችል ምክክር አደረጉ

2 Hrs Ago 24
የአንጎላ የውጭ መረጃ አገልግሎት እና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በደኅንነትና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመሥራት እና የነበሩ ትብብሮችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ የሚያስችል ምክክር አደረጉ

በአንጎላ የውጭ መረጃ አገልግሎት (SIE) ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ማቲያስ በርቲንዶ ማቶንዳ የተመራ የልዑካን ቡድን ለሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የገባ ሲሆን፤ ቡድኑ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ታዜር ገብረ እግዚአብሔር አቀባበል አድርገውለታል።

የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ እና የአንጎላ የውጭ መረጃ አገልግሎት (SIE) በተቋማት ደረጃ በሚከናወኑ የሁለትዮሽና ሀገራዊ ጉዳዮች እንዲሁም በቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለምአቀፋዊ አጀንዳዎች ዙሪያ በስፋት መወያየታቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለኢቢሲ በላከው መረጃ አመልክቷል።

በውይይታቸውም የቀይ ባሕር እና የኤደን ባህረ-ሠላጤ ወቅታዊ ሁኔታዎች፣ በምስራቅ፣ ማዕከላዊ እና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጣና የሚንቀሳቀሱ ሽብርተኛ ቡድኖች፣ የድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች በተለይም መነሻቸውን ከአንጎላ ሉዋንዳ በማድረግ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሚሸጋገሩ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በጋራ ለመከላከል እንዲሁም በአቬዬሽን ሴኩሪቲ ዙሪያ በቀጣይ የሚደረጉ ትብብሮችና የመረጃ ልውውጥ መስኮች ተዳሰዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ታዜር ገብረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ እያከናወነቻቸው የሚገኙ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የፀጥታ ዘርፍ ሪፎርሞች እና ቱርፋቶቻቸውን በሚመለከት ለአንጎላው ልዑክ ገለጻ አድርገዋል።

ኢትዮጵያ በሠላማዊ አማራጮች የባህር በር ተደራሽነትን ለማግኘት የጀመረቻቸውን እንቅስቃሴዎች ለልዑካን ቡድኑ ያስረዱ ሲሆን፤ አንዳንድ አካላት ይህንን ዕውነታ ወደ ጎን በመተው ጉዳዩን ለራሳቸው የፕሮፓጋንዳ ሥራ እየተጠቀሙበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ይህ አካሄድ የአፍሪካ ቀንድ እና የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን ወደ ቀውስ ሊከት እንደሚችል አብራርተው፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ተደራሽነት መረጋገጥ ቀጣናውን እንደሚያረጋጋው እና ኢኮኖሚያዊ ውህደትን ለማምጣት ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል።

የአንጎላ የውጭ መረጃ አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ማቲያስ በርቲንዶ ማቶንዳ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ካላት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት አንፃር ተቋማቸው ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጋር በደኅንነትና ጸጥታ መስኮች የሚያደርገው የልምድና የመረጃ ልውውጥ እንዲሁም በአቅም ግንባታ መስኮች የተጀመሩ የትብብር እና አጋርነት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድገት ያደነቁት አምባሳደር ማቲያስ በርቲንዶ ማቶንዳ፤ ሀገሪቷ በአጭር ዓመታት ውስጥ በዓይን የሚታዩ ትላልቅ የሪፎርም እና የከተማ ልማት ሥራዎችን መስራቷ ለሌሎችም በአብነት የሚወሰድ መሆኑን ገልፀዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የአንጎላ የውጭ መረጃ አገልግሎት (SIE) በደኅንነት እና ፀጥታ ጉዳዮች እንዲሁም በመረጃ ልውውጥ እና ትብብር ሥራዎች ዙሪያ አብሮ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሠነድ መፈራረማቸውን አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ለኢቢሲ የላከው መረጃ ያመለክታል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top