የብሪክስ አባል ሀገራት ባለሐብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ቢያፈስሱ አትራፊ ይሆናሉ:- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

3 Hrs Ago 26
የብሪክስ አባል ሀገራት ባለሐብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ቢያፈስሱ አትራፊ ይሆናሉ:- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሩሲያ ሞስኮ እየተካሄደ ባለው የብሪክስ ቢዝነስ ፎረም ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በአባል ሀገራቱ ያሉ ባለሐብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ቢያፈስሱ አትራፊ እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡

የብሪከስ አባል ሀገራት ወደ ግማሽ የሚጠጋ የዓለምን ሕዝብ ቁጥር ይይዛሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ በፍጥነት እያደገ ያለውን አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) እንደሚይዙ ተናግረዋል።

በዚህ ከፍተኛ አቅምም ብሪክስ ለዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ዕድገት የሚጠቅም ተጨባጭ ለውጥ እና ቀጣይነት ያለው ዕድገት ሊያመጣ እንደሚችል ነው የገለጹት፡፡

ይህን አቅም ወደ ተጨባጭ ሀብት ለመቀየር በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ የመሳተፍ ዕድል ልናገኝ ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚህም ትርጉም ያለውና ዓለምን ወደ ተሻለ መስመር የሚያመጣ ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

የዓለም ፋይናንስ መስራቾች ከታዳጊ ኢኮኖሚ ጋር የሚናበቡ ተቋማትን እንዳልመሰረቱ ጠቁመው፣ በዚህ ምክንያት ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት የሚሠራው ሥራ ላይ እንከን እየተፈጠረ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የፋይናንስ ተቋማት ሁሉንም እኩል ተጠቃሚ የሚያደርጉ መዋቅሮችን እንዲዘረጉ ደጋግመን ጥሪ እያቀረብን ፣ብሪክስም በበኩሉ  የጋራ ተጠቃሚነትን እውን ሊያደርጉ የሚችሉ መዋቅሮችን በአባል ሀገራት መካከል በመዘርጋት ምሳሌ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

ብሪክስ በአባል ሀገራቱ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ታዳጊ ሀገራት ውስጥም ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን እውን ሊያደርጉ የሚችሉ የፋይናንስ ተቋማትን በመዘርጋት ለፍትሃዊ የዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት ምሳሌ ሊሆን እንሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

በፍጥነት እያደገ ያለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለኢንቨስትመንት፣ ለትብብር እና ንግድ ተጨባጭ ዕድሎችን እያመጣ እንሚገኝ ጠቅሰው፤ ይህም በተለይም ለብሪክስ ሀገራት ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ እና ዓለም አቀፍ ገበያ መዳረሻ የሆኑ ከፍተኛ የተፈጥሮ እና የግብርና ሐብት ባለቤት ነች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ይህ ታላቅ ሐብት የአፍሪካ መሪ በሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲደገፍ ደግሞ እጅግ ከፍተኛ ዕድል እንደሚሆን ነው የገለጹት፡፡

በፍጥነት እያደገ ያለው እና አቅምን ያገናዘበው የታዳሽ ኃይል አቅርቦታችን ወጣት እና የሰለጠነ የሰው ኃይል ጋር ሲጣመር ደግሞ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንድትሆን ያደርጋታል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቅርቡ ለንግድ እንቅስቃሴ ተመራጭ የሚያደርጋትን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ሪፎርም ማድረጓን አውስተው፣ ይህም እንደ ቴሌ ኮሙኒኬሽን ያሉ በመንግሥት የተያዙ ቁልፍ ተቋማትን ለግሉ ዘርፍ መክፈትን እንሚጨምር ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቅርቡ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ሥርዓትን መዘርጋቷን አስታውሰው፤ ይህም ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡

እነዚህ ለውጦች የተደረጉት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ገበያ ብቁ ተወዳዳሪ መሆኗን ለማመላከትና ኢንቨስተሮችም ባፈሰሱት መዋዕለ ንዋይ ልክ አትራፊ እንዲሆኑ ለማስቻል መሆኑን ጠቁመው፤ የብሪክስ አባል ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ይህን ዕድል እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የብሪክስ አባል ሀገራት በተለይም ለአፍሪካ ገበያ መዳረሻ ወደሆነችው ኢትዮጵያ መጥተው ለፈጠራ እና ዕድገት እምቅ አቅም ባላቸው በአምራች ዘርፍ፣ ግብርና፣ ታዳሽ ኃይል፣ ማዕድን፣ አይሲቲ እና ቱሪዝም ዘርፎች ኢንቨስት ቢያደርጉ ለጋራ ዕድገታችንም ጠቃሚ ይሆናል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የብሪክስን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና አካባቢያዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ ያለመውን የ2025 የብሪክስ አባል ሀገራት የኢኮኖሚ ትብብር ስትራቴጂን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነችም አረጋግጠዋል፡፡

ይህ ስትራቴጂ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ኢንዱስትሪን ለማሳደግ እና የአካባቢ ጥበቃን ተግባራዊ ለማድረግ ትኩረት አድርጎ ከሚሠራው የኢትዮጵያ የዕድገት ስትራቴጂ ጋር የሚናበብ እንደሆነም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

የብሪክስ አባል ሀገራት አሁን ዓለምን እየፈተነ ያለውን ያልተመጣጠነ ዕድገት፣ ሥራ አጥነት እና ኢ-ፍትሃዊነትን ለመቋቋም የጋራ ስትራቴጂ መቅረጽ እንሚኖርባቸውም አሳስበዋል፡፡

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top