በዓለም አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ የሆኑት "ገንዘብ ለማግኘት ይጫወቱ " (play-to-Earn) ጌሞች መጨመር ትልቅ ለውጥ እያመጣ ነው።
በእነዚህ አዲስ ሃሳብ ይዘው የመጡ ጌሞች ውስጥ፣ ተጫዋቾች መዝናናት ብቻ ሳይሆን በሚጫወቱበት ጊዜ “ክሪፕቶ ከረንሲን” ሊያገኙ ይችላሉ።
በዚህም ምክንያት በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች በዲጂታል ሽልማቶች እና በእነዚህ ልዩ የሆኑ ጌሞች በመሳብ እየጎረፉ ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥም በእንደዚህ አይነት ጌሞች "ገንዘብ ለማግኘት ይጫወቱ " (play-to-Earn) የሚለው ፍላጎት ከፍተኛ እየሆነ የመጣ ይመስላል። ዋናው ግብ ደግሞ “ክሪፕቶ ከረንሲ” ማግኘት ሆኗል።
አሁን ላይ አብዛኛው ማህበረሰብ የተለያዩ “የኤርድሮፕ ገንዘብ ማግኛ ጨዋታዎችን” እንደ ሀምስተር ኮምባት፣ ታፕስዋፕ፣ ሜምፊ ኮይን፣ ኖትኮይን አይነት የገንዘብ ማግኛ መንገዶች ናቸው በማለት “ታብ ታብ” በማድረግ እና የትእዛዝ ስራዎችን በመስራት ገንዘብ ለማግኘት የሚሞክሩ ብዙዎች ናቸው።
ዋናው ነገር እንዲህ አይነት ጌሞች እንደተባለው ገንዘብ ያስገኛሉ ወይ የሚለው ነው?
ኢቢሲ ሳይበር እንዲህ ያለው ገንዘብ ማግኛ “ክሪፕቶ ከረንሲ” እንደሚባለው ገንዘብ ያስገኛል ወይ? የሚለውን ጥያቄ መነሻ በማድረግ ጉዳዩን ከባለሞያዎች እና ከህግ አንጻር ለመቃኘት ሞክሯል።
በጊዜው ጌትነት የማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪ እና የቴክኖሎጂ ባለሞያውነው፡፡ ከኢቢሲ ሳይበር ጋር በነበረው ቆይታ "ገንዘብ ለማግኘት ይጫወቱ" አይነት ጌሞች በንድፈ ሃሳብ ደረጃ የሚሰሩ ቢሆንም የሰዎች አረዳድ ግን ችግር ይፈጥራል ነው የሚለው፡፡
እዚህ ላይ በእርግጥ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት ከተፈቀደላቸው አካላት በስተቀር ከብር ውጪ መገበያየትን አይፈቅድም የሚለውን ህግ ይዘን ጉዳዩን በደንብ እንመልከተው፡፡
"ገንዘብ ለማግኘት ይጫወቱ" የሚሉ ጌሞች እና ገንዘብ ማግኛ መንገዶች ከዲጂታል መገበያያ ውጭ ባሉ እንደ ዶላር አይነት ገንዘቦች ክፍያን እንደሚፈጸም ወይም መለወጥ እንደሚቻል ነው የሚያስተዋውቁት።
የሆነው ሆኖ “ኤር ድሮፕ” የሚባል ሃሳብ መምጣትን ተከትሎ በተለያዩ መንገዶች ማንኛውም ድርጅት የሚሰራበት ስርዓት መሆኑ "ገንዘብ ለማግኘት ይጫወቱ" አይነት ጌሞች የብዙዎችን ቀልብ ስበዋል፡፡
ለዚህ ምሳሌ ነው የሚለው በጊዜው ጌትነት “አንድ ፕሮጀክት ወደ መሬት ሲወርድ ሊያስገኝ የሚችለው ሃብትን በማሰብ ስራው ሳይጀመር ለማስተዋወቅ እና ታዳሚ ለመፍጠር ሲባል “ኤር ድሮፕ” የሚባል ሀሳብ መምጣቱን እና “ኤር ድሮፕ ቃልኪዳን ” እንደማለት ነው ይላል፡፡ ይህም ፕሮጀክቱ መሬት ላይ ሲወርድ ገንዘብ እንሰጣችኋለን እንደማለት ነው በማለትም ያስረዳል፡፡
ፕሮጀክቱን ወደ መሬት ለማወረድ የሚያጋጥሙ የተለያዩ ችግሮችን ለመፍታት ተገልጋዮች “ታብ ታብ” ብቻ በማድረግ በዚህ ሂደት ውስጥ ብዙ ዕይታ ማግኘትን ኢላማ ያደረገ መሆኑንም ባለሞያው ጠቁሟል።
እናም ኮይኖቹ የሚወሰኑት በባለሀብቱ በመሆኑ ጨዋታው ቀድሞ ለመያዝ እንደሆነም አመላክቷል፡፡
ከጨዋታዎቹ መካከል “ሀምስተር ኮምባት” የሚባለው በጣም በርካታ ተከታዮችን በፌስቡክ፣ በቴሌግራም ያፈራ ሲሆን በዩቲውብ ብቻ ወደ 30 ሚሊዮን ተከታዮችን ማፍራት ችሏል።
ይህ ፕሮጀክት ባይሳካ ቢያንስ ብዙ ተከታዮችን በማፍራታቸው ኪሳራ አይገጥማቸውም ይላል በጊዜው ጌትነት።
እንዲህ አይነት ፕሮጀክት አዋጭ ከሆነ ሲጫወቱ ወይም የትዕዛዝ ስራዎችን ሲሰሩ ለነበሩት ሰዎች ክፍያው ሊፈጸም ወይም ኪሳራ ከገጠመ ጨዋታው ጨዋታ ብቻ ሆኖ ሊቀር እንደሚችልም ነው ባለሞያው የሚናገረው።
በመሆኑም እውነት ነው ወይም ውሸት ነው ለማለት ከባድ ነው የሚለው ባለሞያው በመሆኑ ሰዎች ሙሉ በሙሉ እዛ ነገር ላይ ትኩረት ማድረግ ሳይኖርባቸው ግን ደግሞ መሞከራቸው ተገቢ እንደሆነ ነው የሚመክረው።
የሶፍትዌር ባለሞያ እና ተመሳሳይ ጌሞችን የመጫወት ልምድ ያለው ብሩክ ሃብታሙ “ኮይኖች በየጊዜው ፈንድ ይደረጋሉ በማለት ያስረዳል።
የተማከለ ስርዓት ያለውን የባንክ ስርዓት ወዳልተማከለ የመገበያያ ስርዓት የመቀየር ዓላማም ጭምር ያለው ስለመሆኑም ነው የሚገልጸው፡፡
ከእነዚህ ውስጥ ፈርቀዳጅ የሚባለው “ቢት ኮይን” ሲሆን አሁን ደሞ እንደ “ኖት ኮይን” እና ሌሎችም ኮይኖችን መሰረት ያደረጉ ጨዋታዎች ይፋ ተደርገዋል። ይህንኑ ኮይን ለማግኘትም ብዙዎች “ታብ ታብ” በማድረግ ገንዘብ ለማግኘት ይጥራሉ ሲልም ተናግሯል፡፡
አሁን የመጡት እንደ “ሀምስተር ኮምባት”፣ “ታፕስዋፕ” አይነት “ኤርድሮፖች” ሁሉም ልክ እና ክፍያ ይፈጽማሉ ማለት አለመሆኑን ጠቁሟል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የማህበራዊ ገጽ ሆኖ እያገለገለ ያለው ቴሌ ግራም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደሌሎች አማራጮች ገንዘብ መስራት እንዲችል “ቴሌግራም ዋሌት” ብሎ አስተዋውቋል።
ይህ መምጣቱ “ኤር ድሮፕ” የሚለቀቅበትን መንገድ ቀላል እንዲሆን አድርጎታል የሚለው ብሩክ ግዙፍ የዲጂታል ቢዝነስ ጽንሰ ሃሳብ መሆኑን ነው የገለጸው።
ለምሳሌም ይላል ባለሞያው “ቤትኮይን” ትልቅ ማህበረሰብ ገንብቷል፣ የተለያዩ ስራዎችን ሰርቷል፣ የዶላር ዋጋ ወጥቶለት በዓለም ላይ እየተገበያየበት ይገኛሉ፡፡
በእርግጥ “ቢትኮይን” በብዙ ሀገራት ህጋዊ የመገበያያ ገንዘብ እንዳይሆን ክልከላ ቢያሳልፉም በጊዜ ሂደት ጉዳዩን በማጤን የፈቀዱ ሀገራትም እየመጡ ነው።
“ቢትኮይን” እና መሰል ዲጂታል ገንዘብ ሥራ ላይ እንዲውል መፍቀድ የባንክ ሥርዓትን የሚያዛባ ብሎም ሙሉ የባንክ ስራን ከተለመደው ሂደት በማውጣት የገንዘብ ባለቤቶች የማይታወቁ እና ህቡዕ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ።
ይሁን እንጂ ሳይፈቀድም የዲጂታል ገንዘብ ዝውውር በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ መምጣቱ ሀገራት ጉዳዩን በማጤን ህግ በመከለስ እና አዳዲስ ህጎችን በማውጣት በባንክ ስርዓት ውስጥ እንዲካተቱ በማድረግ ከጊዜው ጋር አብሮ ለመጓዝ እየሞከሩ ነው።
የሶፍትዌር ባለሙያው ብሩክ እንደሚለው ለምሳሌ ወደ 12 ሚሊዮን “ታብ ታብ” አድርጌ በኔት ኮይን ወደ 450 ዶላር ሰርቻለው። ነገር ግን ሁሉም ተመሳሳይ የይጫወቱ ያገኙ ወይም “ታብ ታብ” የሚደረጉ ትክክል ናቸው ማለት አይቻልም ነው የሚለው።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ባወጣው መረጃ መሰረት የኢትዮጵያ ህግ ክሪፕቶን በተመለከተ ቃል በቃል የሚለው ነገር የለም፡፡ የኢትዮጵያ መገበያያ ብር ብቻ ነው።
ከብር ውጪ ግብይት መፈጸም ህገወጥ ነው፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት ከተፈቀደላቸው አካላት በቀር ከብር ውጪ መገበያየት ፈፅሞ የተከለከለ መሆኑን ባንኩ ያስረዳል፡፡
እንደዚህ አይነት ህግ ቢኖርም በተለይ ቴሌግራምን መሰረት ያደረጉ ይጫወቱ ያግኙ ጨዋታዎች በስፋት እየታዩ አንዳንዶች ገንዘብ አግኝተናል የሚሉበት ብዙዎች ደግሞ ማድረግ ገንዘብ ያስገኛል ስለተባለ ብቻ የሚያደርጉም ሆነዋል።
ክሪፕቶ ያለው ሰው እንደገንዘብ የመጠቀም፣ የማምረት እና የመሸጥ ወይም የመግዛት መብት ቢኖረውም ይህ ሲደረግ ግብር የማይከፈልበት በመሆኑ የተከለከለ ነው፡፡
ይህንን ያማከለ የተደነገገ ህግ ባለመኖሩ ማንም ሰው በክሪፕቶ የሚያደርገው ግብይት ላይ ለሚፈጠሩ ችግሮች ሁሉ ሃላፊነቱን የሚወስደው ግለሰቡ ብቻ ነው።
በሜሮን ንብረት