የጉምሩክ ኮሚሽን ከየካቲት 21 እስከ 27 ቀን 2017 ዓ.ም ባደረገው ክትትል 573.7 ሚሊዮን ብር የገቢ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች እና 365.3 ሚሊዮን ብር የወጭ ፤ በድምሩ 939 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መያዛቸውን አስታውቋል፡፡
በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መካከል የተለያዩ ማዕድናት፣ አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ ጥራጥሬ፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫ፣ የመዋቢያ ዕቃዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣ መድኃኒት፣ የቁም እንስሳት እና የውጭ ሀገር ገንዘቦች እንደሚገኙበትም ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን በመያዝ ሞያሌ፣ አዋሽ እና አዲስ አበባ ኤርፖርት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙ ሲሆን በቅደም ተከተላቸውም 457 ሚሊዮን፣ 123 ሚሊዮን እና 99 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን መያዝ መቻላቸውን ኮሚሽኑ አስታወቋል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን በህግ ማስከበር ሥራው ላይ ለተሳተፉ የኮሚሽኑ ሰራተኞች እና አመራሮች፣ የክልል እና የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም መላውን ሕዝብ አመስግኗል፡፡
የኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ የአፈጻጸም ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታት ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡