ለኢትዮጵያ ሰላም ከዚህ ቀደም ያልሞከርነውን መንገድ መሞከር ያስፈልጋል፡ - የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች

1 Day Ago 145
ለኢትዮጵያ ሰላም ከዚህ ቀደም ያልሞከርነውን መንገድ መሞከር ያስፈልጋል፡ - የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች

የኢትዮጵያን ሰላም ለመመለስ እና የጋራ መግባባትን ለመፍጠር ከዚህ በፊት ያልሞከርነውን የምክክር መንገድ መሞከር ያስፈልጋል ሲሉ በሀገራዊ ምክክሩ የፌዴራል ተቋማት እና ማኅበራት የምክክር መድረክ ተሳታፊዎች ተናገሩ፡፡ 

ለኢቢሲ ዶትስትሪም ሀሳባቸውን የሰጡት በመድረኩ የተሳተፉት የሲዳማ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ፋንታዬ ከበደ እንዳሉት የምክክር መድረኩ ለኢትዮጵያ ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው፡፡

እርሳቸው በተሳተፉበት መድረክ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች እና የመንግሥት አካላት ተገኝተው የአጀንዳ ግብዓት ማበርከታቸውን የጠቀሱት ወ/ሮ ፋንታዬ፣ ሁሉም ሳይገደብ ሃሳቡን መግለጹን ተናግረዋል፡፡ 

አጀንዳ የሚሰጡት በየመድረኮቹ የሚሳተፉ ብቻ እንዳልሆኑ የጠቀሱት አፈ-ጉበኤዋ፣ ኮሚሽኑ ዜጎች መያዝ አለባቸው የሚሉትን አጀንዎች በስልክ፣ በኢ-ሜይል፣ በፖስታ እና በሌሎች የመገናኛ መንገዶች ሁሉ እንዲሰጡ ማመቻቸቱ ሁሉም ጉዳዮች እንዲዳሰሱ ዕድል እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡

እስካሁን በጦርነት ያልተሞከረ ነገር እንደሌለ ያስታወሱት ወ/ሮ ፋንታዬ፣ ከዚህ በኋላ የሚያዋጣን እና በትኩረት ሊሠራበት የሚገባው የምክክር መንገዱ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

የሰላም መንገድ አዋጭ እንደሆነ ከፕሪቶሪያ ስምምነት መማር እንደሚቻል ጠቁመው፣ ቅሬታዎቻችን ወደ ጠረጴዛ አምጥተን ከተወያየንባቸው ለኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ የሚጠቅም መንገድን እንቀይስበታለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ጀማል አባገሮ በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ምክክሩን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለረጅም ጊዜ በጉጉት ሲጠብቀው እንደነበር ገልጸዋል ፡፡

አሁን ይህ ዕድል ተገኝቶ ጥያቄዎቹ በስፋት እየተነሱ ስለሆ የመጨረሻው አፈጻጸም ላይ ትኩረት በማድረግ ለውጤታማነቱ መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ 

በእርሳቸው በኩል የወከሉትን ማኅበር ጥያቄዎች በየደረጃው ማንሳታቸውን ጠቅሰው፣ ኮሚሽኑ እነዚህ የተነሱ የጋራ ጉዳዮችን ወደ ጠረጴዛ አምጥቶ የመጨረሻ መፍትሔ እንዲያመጡ የማድረግ ታለቅ ኃለፊነት አለበት ብለዋል፡፡ 

ኢትዮጵያውን እንዳይስማሙ የሚያደርጉ ጉዳዮች የትርክት እና ታሪክ መደበላለቅ መሆኑን ያወሱት አቶ ጀማል፣ እነዚህ ሕዝብን የሚያስኮርፉ ጉዳዮች ወደ ፊት መጥተው ውይይት ስላልተደረገባቸው የችግር ምንጮች ሆነው ቆይተዋል ብለዋል፡፡

አሁን በተጀመረው ሀገራዊ ምክክር እነዚህ ጉዳዮች ሁሉ ወጥተው አጀንዳ ስለተደረጉ ተወያይተንባቸው በይቅርታ የሚታለፉት በይቅርታ ታልፈው ወደ ፊት መጓዝ አለብን ብለዋል፡፡

ምክክሩ የተሟላ እንዲሆን የትግራይ ክልልን ጨምሮ ሌሎች በተለያየ ምክንያት ያልተሳተፉ አካላት ተሳታፊ እንዲሆኑ ዕድል መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፣ መንግሥትም ማኅበረሰቡም ለስኬቱ አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡ 

በምክክር መድረኩ ሁሉም መነሳት የሚገባቸው ጉዳዮች መነሳታቸውን የነገሩን ደግሞ በመድረኩ የተሳተፉት አባገዳ ግርማ ገላና ናቸው፡፡

በመድረኩ ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍሎች እና ተቋማት የወከሉ አካላት መሳተፋቸውን ያወሱት አባገዳ ግርማ፣ የተነሱ ሀሳቦችም ቁርሾ ካለ አስወግደው አንድነታችንን ሊያፀኑ የሚችሉ ናቸው ብለዋል፡፡ 

ሁሉም ሰው አንድ የራሱን ሀሳብ ብቻ ይዞ የራሱን ችግር ብቻ ማቀንቀን ሳይሆን የሌላው ወገኑን ችግርም እንደራሱ ችግር መመልከት አለበት ብለዋል አባገዳ ግርማ፡፡

የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች፣ መንግሥት እና ሁሉም የሀገሩ ጉዳይ የሚያሳስበው ወገን ለምክክሩ ተፈጻሚነት የየራሱን ሚና መወጣት አለበት ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በለሚ ታደሰ

#EBC #Ebcdotstream #EthiopianNationalDialogue


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top