የዘረመል ምህንድስና ተስፋ ወይስ ስጋት?

1 Day Ago 138
የዘረመል ምህንድስና ተስፋ ወይስ ስጋት?

የዘረመል ምህንድስና ከእፅዋትና እንስሳት የሚፈለገውን የዘረመል ቅንጣት በመውሰድ ከሌሎች ከማይዛመዱት ዘረመሎች ጋር በማቀናጀት ዝርያን የማሻሻል ሂደት ነው።

ይህም በጀነቲክስ የተሻሻሉ አካላት ልውጠ ህያዋን (GMO) ሲባሉ አጠቃላይ ዘዴው ደግሞ የዘረመል ምህንድስና (Genetic Engineering) ይባላል።

በዚህም መንገድ በርካታ ለምግብና ለአግሮ-ኢንዱስትሪ የሚውሉ ሰብሎች ላለፉት 25 ዓመታት በዓለም ላይ በተለያየ መልክ ተሻሽለው ለገበያ ቀርበው ጠቀሜታ ላይ  ውለዋል።

ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጀታ በረሃማ የአየር ንብረትና ነፍሳትን የሚቋቋሙ የአዝርዕት ዘሮችን በማግኘታቸው የአሜሪካን ብሔራዊ የሳይንስ ሜዳሊያ ሽልማትን ከፕሬዚደንት ጆ ባይደን እጅ መቀበላቸው ይታወሳል።

ለዚህ ሽልማት ያበቃቸው ደግሞ የዕፅዋት ዘረመል ምህንድስና በመጠቀም ያከናወኑት ምርምር ነው። 

ከዚህ ጋር ተያይዞ በጀነቲክስ የተሻሻሉ ልውጠ ህያዋንን (GMO) በዕፅዋት ላይ ብንጠቀም እንደሀገር እንጠቀማለን የሚሉ እና ይህ አሰራር ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ስለሚያይል አያስፈልገንም የሚሉ መከራከሪያዎች ይቀርባሉ።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በጀነቲክስ የተሻሻሉ ልውጠ ህያዋንን (GMO) በዕፅዋት ላይ ብንጠቀም እንደሀገር እንጠቀማለን የሚሉ እና ይህ አሰራር ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ስለሚያይል አያስፈልገንም የሚሉ መከራከሪያዎች ይቀርባሉ። ኢቢሲ በአዲስ  ቀን የሀገር ጉዳይ መሰናዶው በጉዳዩ ላይ እንግዶችን ጋብዞ አነጋግሯል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨረሲቲ የዕፅዋት ባዮ ቴክኖሎጂ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ጥልዬ ፈይሳ፤ በጀነቲክስ የተሻሻሉ ልውጠ ህያዋን (GMO) ቴክኖሎጂን በግብርና ላይ ብንጠቀመው በተለይ በድርቅ፣ በተባይና በአረም ለሚጠቁ ዕፅዋት መፍትሔ እናገኛለን ይላሉ። 

በዓለም ላይ እ.አ.አ. በ2024 ብቻ 210 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ላይ በዘረመል ምህንድና ሒደት የታገዙ ምርቶች መልማታቸውን አንስተው፤ አሜሪካ በሰፊው እየተጠቀመችበት መሆኑን አንስተዋል።

እኛ ደግሞ በምግብ እራሳችንን ለመቻል  ከየትኛውም በላይ ለሀገራችን ልትጠቀምበት የሚገባ ቴክኖሎጂ ነው ሲሉ አስረድተዋል። 

በተለይ ድርቅ በሚከሰትበት ወቅት እስከ 20 ሚሊዮን ሕዝባችን ለእርዳታ ሊጋለጥ ይችላል፤ በዚህ ረገድ ቴክኖሎጂውን ተጠቅመን ድርቅን እና የተለያዩ የግብርና ችግችን መቋቋም የሚችሉ ሰብሎችን ብናመርት አይነተኛ መፍትሔ ይሁነናል ብለዋል። 

የግብርና ምርምርና ልማት ተመራማሪው ፀደቀ አባተ በበኩላቸው (ዶ/ር)፤ በሀገራችን የሚከናወኑ በጀነቲክስ የተሻሻሉ አካላት ልውጠ ህያዋን (GMO) ምርቶችን እንደማይደግፉ ተናግረዋል።

ውጤቱ በአካባቢ ላይ በተለይም ሀገር በቀል ሰብሎችን ሊበክል የሚችል አደጋ እንዳለው አንስተው፤ ከዚህ የተሻለ በመደበኛው መንገድ የተዳቀሉ ምርጥ ዘሮች አሉን እንሱን መጠቀም ይገባል ብለዋል።

በተለይ ከዘረ መል ምህንድስና ውጪ ባሉ መንገዶች የወጡ የበቆሎ ምርምር ውጤቶችን መጠቀም የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኝ አንስተዋል።

ከምግብ ሰብሎች ባለፈ ጥጥን  በተመለከተም ሆነ በሌሎች ምርቶች ላይ መልስ ሊሰጡ የሚችሉ የምርምር ውጤቶች አሉን ያሉት ተመራማሪው፤ በጀነቲክስ የተሻሻሉ አካላት ልውጠ ህያዋን ቴክኖሎጂን መጠቀም ለእኛ ‘ሳይቸገሩ ጤፍ ብድር’ እንደሚባለው ነው ብለዋል።

በዚህ ሃሳብ የማይስማሙት ፕሮፌሰር ጥልዬ ፈይሳ በጀነቲክስ የተሻሻሉ አካላት ልውጠ ህያዋን ምርቶች በሰው ልጅ ላይ ተጽዕኖ እንደሌላቸው ሳይንቲስቶች በሰፊው ያጠኑት ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

በጌትነት ተስፋማርያም

#EBC #Ebcdotstream #GMO #Agriculture


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top