ከቤታቸው በመሥራት እስከ 2 ሺህ ዶላር ተከፋይ መሆኑ ይቻሉ ወጣቶች

6 Hrs Ago 2598
ከቤታቸው በመሥራት እስከ 2 ሺህ ዶላር ተከፋይ መሆኑ ይቻሉ ወጣቶች

የመንግሥት ብሎም በግል የሥራ ዘርፍ ላይ ያሉ ዜጎች በ5 ሚሊዮን ኮደሮች ኢንሼቲቭ ራሳቸውን ሊያበቁ እንደሚገባ በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ስዩም መንገሻ ታቼ ገለጹ።

ዓለም በፈጣን የቴክኖሎጂ ዕድገት ላይ ትገኛለች ያሉት መሪ ሥራ አስፈፃሚው ከለውጡ እኩል መጓዝ የሚችል ዜጋ ማፍራት እንደሚገባም በኢቢሲ አዲስ ቀን የዜና መሰናዶ ላይ ተናግረዋል።

ከዓመታት በኋላ እንደመሠረታዊ የትምህርት ማስረጃዎች ሁሉ የሥልጠናው ሠርተፊኬት የመለኪያ መስፈርት እንደሚሆንም ነው ያስረዱት።

የኢንተርኔት አገልግሎት አስቸጋሪ በሚሆንባቸው የክልል ከተሞች ያሉ ዜጎች በምን መልኩ ታሳቢ ተደርገዋል? ሲል ኢቢሲ ጠይቋል።

መሪ ሥራ አስፈፃሚው አቶ ስዩም ለዚሁ በሰጡት ምላሽ፣ የኢንተርኔት አገልግሎት አስቸጋሪ በሆነባቸው አካባቢዎች ያሉ ዜጎች የዕድሉ ተጠቃሚ አንዲሆኑ በማሰብ ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም የበይነ መረብ ሥልጠናው ለሁሉም ዜጋ ተደራሽ እንዲሆን ያለምንም ክፍያ የሞባይል ዳታ በማብራት ብቻ በድኅረ-ገጹ ያሉ ትምህርቶችን መውሰድ እንዲቻል መደረጉን አመላክተዋል።

እንዲሁም በአካባቢዎቹ ላይ ካሉ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በመነጋገር ኮምፒዩተሮችን መጠቀም እንዲችሉ መደረጉን ጠቅሰዋል።

እንደ ማኅበረሰብ የበይነ መረብ ትምህርት አወሳሰዳችን ብዙ እንደሚቀረው ገልጸው፣ ኢኒሼቲቩ ይህን ለመቅረፍ ሥር-ነቀል የለውጥ እንቅስቃሴ እንደሚያስፈልግ የተገነዘብንበት ነው ሲሉ አስረድተዋል።

በዚህም በሥልጠናው ብቁ የሆኑ ዜጎች ገና እየጀመሩ ያሉትን የሚያግዙበት ዕድል መመቻቸቱን አንሥተዋል።

በተጨማሪም ግንዛቤ የማስጨበጥ እና የማበረታታቱ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል በማለት በዚህ ሂደት ውስጥ ሚዲያዎች ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በሁሉም ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች እየተሰጠ የሚገኘው የ5 ሚሊዮን ኮደሮች ኢኒሼቲቭ ለወጣቶች የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ደግሞ በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ፕሮጀክት ኃላፊ የሆኑት አቶ ብርሃኑ አለቃ ገልጸዋል።

በኢኒሼቲቩ በቴክኖሎጂ የሠለጠኑ እና የበቁ ዜጎችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ላሉ የሥራ ዕድሎች ተሳታፊ ማድረግ መቻሉን ነው ያስታወቁት።

አክለውም መንግሥት በቁርጠኝነት ዜጎችን ለማብቃት ይህን እንቅስቃሴ ባይጀምር ዓለም ከደረሰበት መሠረታዊ የአይሲቲ እውቀት ወደ ኋላ የቀረን እንሆን ነበር ይላሉ።

ሥልጠናውን ተከትሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር 95 ሺህ የሥራ ዕድሎች ለዜጎች መመቻቸቱንም አንስተዋል።

በዚህም 50 ሺህ በሚሆነው የሥራ ዘርፍ ላይ ዜጎች ተሳታፊ መሆናቸውን የገለጹት የፕሮጀክት ኃላፊው፣ ሥራዎቹ በወር እስከ 2 ሺህ ዶላር ተከፋይ የሚያደርጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በቀጣይ 250 ሺህ የሚሆኑ የሪሞት (የርቀት) የሥራ ዕድሎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማምጣት ስምምነቶች እየተደረጉ መሆናቸውንም አያይዘው ተናግረዋል።

የኢንሼቲቩ ተጠቃሚ ወጣቶች በበኩላቸው የ5 ሚሊዮን ኮደሮች ኢኒሼቲቭ የዓለም አቀፍ የሥራ ዕድሎች ተጠቃሚ ለመሆን እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

ይህን መሰል ዕድል በራስ መተማመንን እና ገቢን ከማሳደግ ባሻገር ሕይወትን የሚያቀልል መሆኑንም ነው የገለጹት።

በሥልጠናው ማብቂያ በሚወስዱት የብቁነት ማረጋገጫ በመደበኛ ብሎም ተጨማሪ ገቢ ማስገኘት በሚችሉ የሥራ ዘርፎች ላይ እንድንሰማራም አስችሎናል ብለዋል።

በአፎሚያ ክበበው


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top