የፌዴራል ዋና ኦዲተር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን የስራ አፈጻጸምና የ2016 በጀት ዓመት የሒሳብ እንቅስቃሴዎችን ኦዲት አድርጓል።
የኦዲት ሪፖርቱ ሰሞኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበ ሲሆን፤ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ ፌዴሬሽኑ በተለይ ከአዲዳስ ኩባንያ ጋር በተያያዘና ከዶላር ሒሳብ ጋር ያጋጠሙ ጉድለቶችን አቅርበዋል።
ፌዴሬሽኑ ከአዲዳስ ስፖርት ካምፓኒ ጋር እ.ኤ.አ ከጃንዋሪ 1/2013 እስከ 31 ዲሴምበር 2020 ድረስ የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ማድረጉን ወይዘሮ መሰረት አስታውሰዋል።
በተደረገው ኦዲት ፌዴሬሽኑ በገባው ውል መሰረት ከአዲዳስ ካምፓኒ ለሚገቡ ትጥቆች ፌዴሬሽኑ የትራንዚትም ሆነ ሌሎች ተያያዥ ወጪ ሳያወጣባቸው (Free Charge) እንደሚያቀርብ የተጠቀሰ ቢሆንም፤ ፌዴሬሽኑ ግን ከአዲዳስ ካምፓኒ የመጡ ትጥቆች ለትራንዚትና መጋዘን ወጪ ከ2014 ዓ.ም እስከ 2016 ዓ.ም በድምሩ ከ3 ሚሊዮን 588 ሺህ ብር በላይ መክፈሉ ተረጋግጧል ብለዋል።
ከዚህ ውስጥ ብር 1 ሚሊዮን 835 ሺህ 882 ብሩ ለምን ጉዳይ እንደተከፈለ ማስረጃ እንዳልቀረበ አስታውቀዋል።
በተጨማሪም፤ በየዓመቱ በስልጠና ፕሮጀክቶች ስር ለሚገኙ ለ1200 ታዳጊ አትሌቶች 11 አይነት ትጥቶች እንደሚላክላቸው በውል ቢቀመጥም ፌዴሬሽኑ ግን የሚልካቸው የትጥቅ አይነቶች 6 ብቻ መሆናቸውን ዋና ኦዲተሯ ገልጸዋል።
ይህም ብቻም አይደለም ፌዳሬሽኑ ከአዲዳስ ካምፓኒ ጋር በገባው ውል መሰረት ከካምፓኒው በየዓመቱ የተላከለትን የዶላር መጠን የሚያሳይ ከካምፓኒው የተላከ ማስረጃ አልተገኘም ብለዋል።
ዶላሩ የሚገባበት የፌዴሬሽኑ የውጭ ምንዛሬ አካውንቶች ብዛት ስንት እንደሆነ እና ኦዲት ስለመደረጋቸው የሚያሳይ ማስረጃ ተጠይቆ ፌዴሬሽኑ አለማቅረቡን ዋና ኦዲተሯ ተናግረዋል።
በተያያዘም የፌዴሬሽኑ የዶላር ገንዘብ የተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማት በኢትዮጵያ ብር ለመቀየር በመስማማት የሚለዋወጡ ሲሆን፤ አጠቃላይ ለግለሰቦችና ለተቋማት በብር እንዲቀየር ትዕዛዝ የሚሰጥ መሆኑን ዋና ኦዲተሯ አስታውቀዋል።
ዶላሩ ወደብር ከተቀየረ በኋላም በህጋዊ ደረሰኝ ወደ ፌዴሬሽኑ አካውንት ገቢ ስለመደረጉ ወይም በተሰብሳቢ መልክ ስለመያዙ ሪፖርት አለመቅረቡንም አስታውቀዋል።