በቅርቡ ወደ ሥልጣን የመጡት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (USAID) ለሦስት ወራት ሥራ እንዲያቆም ትዕዛዝ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር የእንግሊዝ ተራድኦ ድርጅት (UKAID) የበጀት ማስተካከያ በማድረግ በዚሁ ድርጅት በኩል ለውጭ ሀገራት ከሚደርገው እርዳታ በመቀነስ የመከላከያ በጀታቸውን በ2.5 በመቶ ለማሳደግ መወሰናቸውን አስታውቀዋል፡፡
የእነዚህ ተራድኦ ድርጅቶች ሥራቸውን ማቆም በተለይ በአፍሪካ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳለው በርካቶች እየተናገሩ ነው፡፡
የእርዳታው መቋረጥ በኢኮኖሚ እድገት፣ በጤና፣ በደኅንነት፣ በአስተዳደር እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር የሚናገሩ አልጠፉም።
የአፍሪካ ሀገራት ራሳቸውን ለመቻል እየጣሩ ቢሆንም በውጭ እርዳታ መቀነስ ለሰብዓዊ ቀውስ ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም ነው እየተገለጸ ያለው።
የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ባወጣው መግለጫ የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (USAID) እርዳታውን በመቀነሱ ምክንያት ስምንት ሀገራት የኤች አይ ቪ (ሴድስ) መድሃኒቶችን ሊያጡ እንደሚችሉ አስጠነቅቋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) በበኩሉ የገንዘብ ድጋፉ መቋረጥ በርካታ የኮሚሽኑ ፕሮግራሞች እንዲዘጉ ምክንያት እንደሆነ አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የእርዳታዎቹ መቋረጥ ለአፍሪካ የማንቂያ ደወል መሆን እንዳለበት የሚሟገቱ ደግሞ እየተበራከቱ ነው። በዚህ በኩል የሚነሳው ሚዛን አፍሪካ የከፈለችውን ዋጋ ከፍላ ከእርዳታ ለመላቀቅ የምታስብበት ጊዜ መሆኑን በማንሳት ነው፡፡
በአሜሪካ የአፍሪካ ሕብረት የቀድሞ አምባሳደር ቺሆምቦሪ-ኩዎ ይህን ጉዳይ አስመልክተው ከአልጀዚራ "The Bottom Line" ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቆይታ የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (USAID) በአፍሪካ ውስጥ “የበግ ልብስ የለበሰ ተኩላ” ነበር ይላሉ፡፡ ሌሎች የተራድኦ ድርጅቶችም ተመሳሳይ እንደሆኑ ነው አምባሳደሯ የሚያወሱት፡፡
እነዚህ የተራድኦ ድርጅቶች በወረቀት ላይ የመንግሥት የአገልግሎት ክፍተትን ለመሙላት፣ የጤና ዘርፉን ለመደገፍ፣ የትምህርት ዘርፍን ለማሳደግ እና ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ እንደመጡ ቢገልጹም ይህ ግን ሽፋን ነው ይላሉ፡፡
ሀሳባቸውን ለመደገፍም፣ "እነዚህ ድርጅቶች የጤና እና የትምህርት ዘርፍን ለማሻሻል እንደመጡ ይገልጻሉ፤ ነገር ግን በዚህ ረገድ የመጣ ለውጥ የት አለ? እስቲ በእነሱ እርዳታ የጤና እና የትምህርት ዘርፉን ያሻሻለ አንድ ሀገር ጥራልኝ?" በማለት ነው ጋዜጠኛውን መልሰው የሚጠይቁት፡፡
የአሜሪካ ታክስ ከፋዮች ከነሱ የሚሰበሰበው ቢሊዮን ዶላር አፍሪካን ለመርዳት ይውላል ብለው ቢያምኑም እውነታው ግን ለታለመለት ተግባር የሚውለው በጣም ጥቂቱ መሆኑ ነው ይላሉ አምባሳደር ቺምቦሪ-ኩዎ፡፡
ድርጅቶቹ የአፍሪካን ግብርና እናሻሽላለን ብለው ቢመጡም የዘረ መል ማሻሻያ የተደረገባቸውን ዘሮች በማሰራጨት የአፍሪካን ግብርና እንዳዳከሙ ይገልጻሉ፡፡
የአፍሪካ መሪዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ቆም ብለው ማሰብ አለባቸው የሚሉት አምባሳደሯ፣ ወስነው ከሠሩ በውጭ እርዳታ የሚሸፈነውን በጀት ራሳቸው መሸፈን ይችላሉ በማለት ይከራከራሉ፡፡
አፍሪካ ረሷን ቆም ብላ ካየች ሰጪ እንጂ ለማኝ አይደለችም የሚሉት አምባሳደር ቺምቦሪ-ኩዎ፣ የበለፀጉት ሀገራት ከአፍሪካ ጥሬ ዕቃ ባያገኙ ህልውናቸው አደጋ ውስጥ ይገባ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ በተለይም አውሮፓ ያለአፍሪካ ማዕድናት ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት ለማገገም ይሳናት እንደነበር ያወሳሉ፡፡
የእርዳታዎቹ መቋረጥ ለአፍሪካ የማንቂያ ደወል መሆን እንዳለበት ጠቅሰው፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ “ቅድሚያ ለአሜሪካ” እንደሚሉት ሁሉ የአፍሪካ መሪዎችም "ቅድሚያ ለአፍሪካ" ማለት መጀመር አለባቸው ይላሉ፡፡
"አፍሪካ እየሰጠች ለምን ትለምናለች?" በማለት የሚጠይቁት አምሳደሯ፣ አሁን አፍሪካ በትናንሽ ሀገራት ተከፋፍላ ሳይሆን በጠንካራ ሕብረት በዓለም ፊት መቆም አለባት ብለዋል፡፡
እንደ ዓለም ገንዘብ ድርጅ ያሉት ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትም የተመሰረቱት አፍሪካን እና ሌሎች ታዳጊ ሀገራትን ለመርዳት ሳይሆን አውሮፓውያን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንዲያገግሙ እንደሆነ አምባሳደር ቺምቦሪ-ኩዎ ገልጸዋል፡፡
እናም አፍሪካ ከለማኝነት ለመውጣት የተራድኦ ድርጅቶቹን ሥራ ማቆም እንደ ዕድል ተጠቅመው የተፈጥሮ ሀብታቸውን በማልማት ከልመና መውጣ አለባቸው ይላሉ፡፡
በለሚ ታደሰ