የተፈጥሮ ወሰንን ያለፉት የ69 ልጆች እናት - ቫለንቲና ቫሲሊየቭ

1 Day Ago 139
የተፈጥሮ ወሰንን ያለፉት የ69 ልጆች እናት - ቫለንቲና ቫሲሊየቭ

ሰው በተወለደበት ዕለት አልቅሶ በሚሞትበት ዕለት ተለቅሶለት ይሸኛል፡፡ በዚህ ሂደት አራት ብሉ ድሆ፣ ሁለት በሎ ቆሞ ሄዶ ሦስት ብሎ በከዘራ ተደግፎ መጨረሻው ይሆናል፡፡ አድጎ ጎርምሶ፣ ጎልምሶ፣ አርጅቶ፣ አንዱም በደስታ አንዱም በፀፀት ዓለምን ይሰናበታታል፡፡ በዚህ ሂደት ለጉርምስናው፣ ለጉልምስናው፣ እንዲሁም ለእርግናው የጊዜ ገደብ ተበጅቶለታል፡፡

በተለይም ሴቶች ዘር ለመተካት የተወሰነ የዕድሜ ገደብ አላቸው፡፡ ይህ የዕድሜ ገደብ ወደዚህ ዓለም የሚያመጧቸውን እምሳሎቻቸውን ቁጥርም ይገድባል፡፡ ለዚህም ነው አንዲት እናት ስምንት፣ አሥር፣ አሥራ ሁለቱ፣ አሥራ አምስት ድረስ ወለደች ተብሎ እንደ ትንግርት የሚነሳው፡፡

በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኖሩት ሩሲያዊቷ እናት ቫለንቲና ቫሲሊየቭ ግን ይህን የተፈጥሮ ህግ ሽረዋል፡፡ ቫሲሊየቭ በዚህ ምድር ላይ የኖሩት ለ76 ዓመታት ገደማ ነው፡፡

ከዚህ ዕድሜያቸው ውስጥ ከ1725 እስከ 1765 ባለው 40 ዓመታት 27 ጊዜ አምጠው 69 ልጆችን ወልደዋል፡፡ ይህ ነው የተፈጥሮ ወሰንን ያለፉ ያሰኛቸው፡፡

ነገሩስ ለሰሚው ግራ የሚያጋባ ይመስላል! ግን ደግሞ በተለያዩ መንገዶች እውነትነቱን ያረጋገጠው የዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ አስደናቂ ሴት በማለት በባሕረ መዝገቡ አስፍሯቸዋል፡፡

27 ጊዜ አምጠው 69 ልጆች መውለድ እንደምን ይቻላል? ቢሉ ሴትዮዋ፣ በእያንዳንዱ ምጥ እስከ አራት መንታ ተገላግለው እንደሆነ መቀመጫውን ኒውዮርክ ያደረገው እና ልዩ ልዩ አስደናቂ ጉዳዮችን የሚመዘግበው all that's interesting (ATI) የተሰኘ ድረገጽ ታሪኩን መዝግቧል፡፡

ቢቢሲም "The Gentleman’s Magazine" የተባለውን እና ኦገስት 13 ቀን 1782 የታተመውን የሩሲያ መጽሔትን መረጃ ዋቢ አድርጎ ፍዮዶር የተባሉ ሩሲያዊ አርሶ አደር ባለቤት የሆኑት ቫሲሊየቭ ታሪክ እውነት መሆኑን አረጋግጧል፡፡

በዚህ መጽሔት መረጃ መሰረትም ቫሲሊየቭ አራት ጊዜ 4 መንታ አጠቃላይ 16 ልጆች፣ ሰባት ጊዜ 3 መንታ አጠቃላይ 21 ልጆችን፣ 16 ጊዜ 2 መንታ አጠቃላይ 32 ልጆችን እና ቀሪዎቹን ደግሞ አንድ አንድ በመውለድ በድምሩ 69 ልጆችን ወልደዋል፡፡

በዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ መረጃ መሰረት በ1725 የመጀመሪያዎቹን ልጆች፣ በ1765 ደግሞ የመጨረሻቸውን ልጆች የተገላገሉት ሴት፣ በ76 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ከመለየታቸው በፊት ለ40 ዓመታት ወሊድ ላይ ቆይተዋል።

ከሁሉ በላይ የሚደንቀው ደግሞ ቫስሊየቭ ከወለዷቸው ልጆች መካከል 67 ልጆቻቸው በሕይወት መኖራቸው ነው።

የቫስሊየቭን እና ልጆቻቸውን ታሪክ መዝግቦ ያስቀመጠው ኒኮልስክ ገዳም በ1782 ለሞስኮ ባቀረበው ሪፖርት ላይ ከ69 ልጆቻቸው መካከል ሁለቱ ገና ጨቅላ እያሉ መሞታቸውን አመልክቷል።

ይህ እንዴት ሊፈጠር ቻለ? በማለት "ATI" ከብዙ አጋጣሚዎች መካከል በጥቂቱ ሊከሰት እንደሚችል እና ጉዳዩ ከሳይንስ በላይ እንደሆነ ይጠቅሳል፡፡

የስታንፎርድ የማህፀን እና ፅንስ ሕክምና ፕሮፌሰር የሆኑት ቫለሪ ቤከር ይህን ጉዳይ አስመልክተው ለ‘ሂስትሪ ዴይሊ’ በሰጡት ሀሳብ "ተፈጥሮ ለሁሉም ገደብ ያበጃል፤ እርግዝና አንዲት ሴት የምታልፍበት ከሁሉ ይልቅ ከባድ የሆነ የተፈጥሮ ክስተት ነው" ይላሉ፡፡

በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የመራቢያ ሳይንስ እና የሴቶች ጤና ምርምር ክፍል ዳይሬክተር የሆኑት ጄምስ ሴጋርስ በበኩላቸው በፕሮፌሰር ቫለሪ ቤከር ሀሳብ ይስማማሉ። አክለውም፣ "እያንዳንዱ እርግዝና ለእናቲቱ ሕይወት አደገኛ ነው" ይላሉ፡፡  

የሴቶች ሥነ-ተዋልዶ ተመራማሪ የሆኑት በአሜሪካ የሰሜን ምሥራቅ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ጆናታን ቲሊ፣ "እነዚህን ሁሉ መንትያዎች? በጣም አስገራሚ ነው!" ብለዋል፡፡

እነዚህ ተመራማሪዎች ሁሉ ግን የቫስሊየስ 27 እርግዝና እና 69 ልጆችን መውለድ በአጋጣሚ ሊፈጠር የሚችል ነው ከሚለው በላይ ምንም ዓይነት ተጨባጭ ሳይንሳዊ መላ ምት ማምጣት አልቻሉም፡፡

ታዲያ እንዲህ ዓይነቱን ክስተት የተፈጥሮን ወሰን ያለፈ ክስተት ከማለት ውጭ ምን ማለት ይቻላል?

በለሚ ታደሰ 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top