የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከፍተኛ አመራር በሆኑት ጃል ሰኚ ነጋሳ የተመራ የሠራዊቱ አመራሮች የዓድዋ ድል መታሰቢያን እና ሌሎች የልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ከጎበኙ በኋላ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንኳን ወደ ሰላም መንገድ መጣችሁ ብለው ተቀብለዋቸዋል::
በዚሁ ወቅት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የሰላም መንገድ አማራጭ የሌለው እና ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ መንገድ መሆኑን በመረዳት መንግስት ላደረገው ጥሪ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አባላት የሰጡት ምላሽ የሚያስመሰግን መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ስምምነቱ የፖለቲካ እና የሃሳብ ልዩነቶችን ዘመናዊ በሆነ መንገድ በውይይትና በሰላም መፍታት ለሌሎችም አርአያ የሚሆን ተግባር መሆኑን ገልጸዋል::
የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከፍተኛ አመራር ጃል ሰኚ ነጋሳ በበኩላቸው፤ ለተደረገላቸው አቀባበል አመስግነው፤ የሰላም ጥሪውን የተቀበሉት የህዝብን ጉዳት ለመቀነስ እና የሰላም አማራጭን መቀበል ብልህነትና አዋቂነት መሆኑን በመረዳታቸው እንደሆነ ተናግረዋል::
በኦሮሚያ ክልል መንግሥት እና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች መካከል የሰላም ስምምነት መፈራረሙን ተከትሎ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አባላት የዓድዋ ድል መታሰቢያን፣ አንድነት ፓርክን እንዲሁም በአዲስ አበባ የተገነቡ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው መጎብኘታቸውን የከንቲባ ፅ/ቤት መረጃ ያመለክታል::