ከስኬታማ ሕዝባዊ አገልግሎት እስከ ምርጥ የስፖርት ክለብ ፕሬዚዳንትነት የዘለቀው ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ ጉዞ

1 Day Ago 543
ከስኬታማ ሕዝባዊ አገልግሎት እስከ ምርጥ የስፖርት ክለብ ፕሬዚዳንትነት የዘለቀው ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ ጉዞ

ሪያል ማድሪድ በእርሳቸው የፕሬዚዳንትነት ዘመን 7 የአወሮፓ ቻምፕዮንስ ሊግ፣ 7 የስፔን ላሊጋ፣ 7 የስፔን ሱፐርካፕ እና 6 የፊፋ ክለቦች ዓለም ዋንጫን ጨምሮ 36 ዋንጫዎችን አሸንፏል።

ዋናው ሙያቸው ኢንጂነሪኒግ ሲሆን በዚሁ ሙያ ከሕባዊ አገልግሎት እስከ ትልቅ ኩባንያ ፕሬዚዳንትነት የደረሰ አንቱታ አግኝተውበታል።

ከማድሪድ ፖሊቴክኒክ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ኢንጂነሪንግ ተመርቀዋል። የግላቸውን ኩባንያ ከማቋቋማቸው በፊት ከመሠረተ ልማት እና ከከተማ ዕቅድ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ሕዝባዊ አገልግሎቶችን አበርክተዋል።

በማድሪድ ከተማ ምክር ቤት የፅዳት እና የአካባቢ ጥበቃ ተወካይ፣ የኢንዱስትሪ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂ ልማት ማዕከል የፕሮሞሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሠርተዋል።

በትራንስፖርት ሚኒስቴር የትራንስፖርት መሠረተ ልማት ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ሪፎርም እና ልማት ኢንስቲትዩት ፕሬዚዳንት ሆነው ሀገራቸውን አገልግለዋል።

እ.አ.አ በ1983 "ኮንስትራሲዮንስ ፓዶስ" የተባለ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው የግል ሥራ ጀመሩ።

ቀጥለውም "አክቲቪዳዴስ ዴ ኮንስትሩቺዮን ኢ ሰርቪሲዮስ፣ ኤስ ኤ" የተሰኘ የግንባታ ኩባንያ አቋቁመው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆኑ።

ኩባንያውንም ስፔን ካሉት ትልልቅ የግንባታ እና የአገልግሎት ኩባንያዎች አንዱ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የዘርፉ መሪ እንዲሆን አድርገውታል።

አሁንም የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቢሆኑም በስፋት የሚታወቁት ግን በሪያል ማድሪድ የእግር ኳስ ክለብ ፕሬዚዳንነታቸው ነው። 

ከ2000 እስከ 2006 እንዲሁም ከ2009 እስከ አሁን የሪያል ማድሪድ ፕሬዚዳንት ሆነው እያገለገሉ ሲሆን፣ ክለቡ በዓለም ክለቦች ታሪክ ገናና እንዲሆን አድርገውታል። በእግር ኳስ ታሪክ እጅግ ስኬታማ ከሆኑት የክለብ ፕሬዚዳንቶች አንዱ የሆኑት የ78 ዓመቱ ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ በፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው በሳንቲያጎ ቤርናባው የተቀዳጁት ስኬት በክለቡ ታሪክ ከፍተኛው ነው።

በመጀመሪያው የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው "ጋላክቲኮስ" የሚለውን ፖሊሲ በመተግበር ይታወሳሉ።

በዚህ ወቅት እንደ ሉዊስ ፊጎ፣ ዚነዲን ዚዳን፣ ሮናልዶ ናዛሪዮ ዴሊማ፣ ሪካርዶ ካካ እና ዴቪድ ቤካምን የመሳሰሉ ታዋቂ ተጨዋቾችን በማስፈረም የክለቡን ገበያ ከፍ አድርገውታል። እነዚህን ተጨዋቾች ያስማሙባቸው መንገድ ደግሞ ምርጥ ተደራዳሪነታቸውን የሚያሳይ ነው።

በተለይም ዚነዲን ዚዳንን በናፕኪን ላይ በተጻፈ የዝውውር ጥያቄ ከጁቬንቱስ ያስኮበለሉበት እና ሉዊስ ፊጎን ከባርሴሎና የቀሙበት መንገድ በስፋት የሚነገርላቸው ነው። በዚህ ወቅት ክለቡ በሁሉም የዓለም ክፍል በተለይም በእስያ እና አሜሪካ በርካታ ደጋፊዎችን አንዲያገኝ ቢያደርጉም፣ በሜዳ ላይ ግን እምብዛም ውጤታማ አልነበሩም።

ለክበቡ ጤናማ የገንዘብ አጠቃቀም ቅድሚያ ይሰጣሉ። በዚህም የክለቡን እዳ በመቀነስ ሪያል ማድሪድን የዓለማችን እጅግ ባለጸጋ እና ውድ የስፖርት ክለብ እንዲሆን አድርገውታል።

"ሲውዳድ ሪያል ማድሪድ" የተሰኘ ዘመናዊ የሥልጠና ኮምፕሌክስ ግንባታ እና የሳንቲያጎ ቤርናባው ስታዲየምን እድሳትን ጨምሮ ግዙፍ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በበላይነት መርተዋል። እነዚህ ፕሮጀክቶች ከመጫወቻ እና መለማመጃ ቦታነት አልፈው የክለቡን የገቢ ምንጭ በከፍተኛ ሁኔታ አሻሽለዋል።

የሳንቲያጎ ቤርናባው ስታዲየምን ሁለገብ አገልግሎት እንዲሰጥ አድርገው ያደሱበት መንገድ ግን ከሁሉም በላይ የእግር ኳስ ባለራዕይ እና ስትራቴጂስት መሆናቸውን ያረጋገጠ እንደሆነ ይነገርላቸዋል።

በ2009 በተጀመረው የሁለተኛው ዙር የፕሬዚዳንትነት ጊዜያቸው የ"ጋላክቲኮ" ፖሊሲያቸውን ቀይረው ባለተሰጥኦ እና አዳጊ ተጨዋቾችን ወደ ክለቡ በማምጣት ላይ አተኩረዋል። እንደ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ፣ ሉካ ሞድሪች፣ ጋሬዝ ቤል፣ ካሪም ቤንዜማ እና ቶኒ ክሮስ ያሉ ተጨዋቾችን በማስፈረም ክለባቸውን አጠናክረዋል። እንደ ቪኒሽየስ ጁኒየር፣ ሪድሪጎ፣ ቫልቬርዴ እና ሌሎች ባለተሰጥኦዎችን በማስፈረም ውጤታማ ሆነዋል።

ይህ ወቅት ከፍተኛ ስኬት ያስመዘገቡበት ነው። በተለይም በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ በ12 ዓመታት 6 ዋንጫዎችን (ከ2016 እስከ 2018 ያለውን ሦስት ተከታታይ ድልን ጨምሮ) በማሸነፍ ታሪክ ሠርቷል።

ፔሬዝ በስትራቴጂክ አስተሳሰባቸው እና ለክለቡ የረጅም ጊዜ ራዕይ በመቅረጽ ይታወቃሉ። ክለቡን የሚፈልገውን የትኛውንም ተጨዋች በማስፈረም፣ እንዲሁም ምርጥ ክለቦች ብቻ የሚሳተፉበት የአውሮፓ ሱፐር ሊግ እንዲፈጠር አዋዛጋቢ ሀሳቦችን በማቅረባቸው ይታወቃሉ። የክለቡን ተፅዕኖ ለማስቀጠልም ተስፋ ያላቸውን ባለተሰጥኦ ወጣቶች የሚያድጉበት የክለቡን የወጣቶች አካዳሚ አጠናክረዋል።

ክለቡ በውድድር ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ገበያ ላይም ተፅዕኖ ፈጣሪ እንዲሆን አድርገውታል። በተጠናው የክለቡ የቅድመ ውድድር እንቅስቃሴዎች ክለቡ ከፍተኛ ገቢ በማግኘት በጠንካራ መሠረት ላይ እንዲቆም አስችለውታል።

ፔሬዝ በእግር ኳሱ ብቻ ሳይሆን ለሪያል ማድሪድ የቅርጫት ኳስ ክለብም 28 ዋንጫዎችን አስገኝተዋል።

በለሚ ታደሰ

#ebcdotstream #EBC #Football #RealMadrid #Galactico #Perez

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top