ሙዲክ ልክ እንደዛሬው የኢድ አል አድሀና እንዲሁም ኢድ አልፈጥር በዓል ሰሞን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሻንጣቸውን ሸክፈው ወደ ትውልድ መንደራቸው የሚጓዙበት የእስልምና ኃይማኖትን መሰረት ያደረገ የኢንዶኔዥያውያን ባህል ነው።
ጃካርታ ከ10 ሚሊዮን በላይ ሕዝቦች የሚኖሩባት የኢንዶኔዥያ ዋና ከተማ ናት። ታዲያ ይህች ቀን ከለሊት ደምቃ የምትውለውና የምታድረው ከተማ የኢድ አል-አድሀ በዓል ሊከበር ጥቂት ቀናት ሲቀሩት የወትሮ ግርግሯ መቀነስ ይጀምርና ልክ ለበዓሉ ሁለትና ሶስት ቀን ሲቀረው ፈፅሞ ጭር ትላለች።
በምትኩ የአውቶቡስና የባቡር ጣቢያዎች እንዲሁም የአውሮፕላን ማረፊያዎች ትላልቅ ሻንጣ እና የተለያዩ እቃዎችን ይዘው ወደ ትውልድ ከተማቸው በሚሄዱ ሰዎች ይጨናነቃል።
በኢንዶኔዥያ መንገዶች ለረጅም ሰዓት የሚዘጋጋ የትራፊክ መጨናነቅ በተለያዩ ቦታዎች ያጋጥማል ። አንዳንዴ ይህ የትራፊክ መጨናነቅ ለብዙ ሰዓታት ስለሚዘልቅ መንገደኞች በመኪና ውስጥ ለማደር ይገደዳሉ።
ሙዲክ ለኢንዶኔዥያውያን ከቤተሰብና ከአብሮ አደጎቻቸው ጋር ለመገናኘት ለወራት ጓጉተው የሚጠብቁት ታላቅ ቀናቸው ነው።
ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን በዓልን ለማክበር ከተለያዩ ቦታዎች የሚመጡት ሰዎች በሀገር ውስጥ የሚኖሩ ብቻ አይደሉም።
ለሙዲክ በዓል ከማሌዥያ መካከለኛው ምስራቅ አውሮፓና አሜሪካ የሚኖሩ ሁሉ ጉዞ ወደ ሀገር ቤት ብለው ገና ወራት ሲቀር ጀምሮ ሲዘጋጁበት የሚቆዩበት ባህላቸው ነው።
በዚህም ምክንያት ወደ ኢንዶኔዥያ የሚደረጉ በረራዎች በብዙ እጥፍ ቁጥራቸው ይጨምራል ። በሀገር ውስጥ የሚኖሩ ተጓዦችም የሚያጋጥማቸው የትራንስፖርት እጥረት ቀላል አይደለም።
በዚህ ወቅት የትኬት ዋጋዎች በሁለትና በሶስት እጥፍ ይጨምራሉ። የአውቶቡስ፣ የባቡርና የአውሮፕላን ትኬቶች ቀድመው ስለሚሸጡ ትራንስፖርት ለማግኘትም አስቸጋሪ ነው። ሆኖም ሁሉንም ነገር ተቋቁመው፤ በዓልን ከናፈቁት ቤተሰብና ወዳጅ ዘመድ ጋር ለማክበር ይጓዛሉ።
ምክንያቱም ይህ ሙዲክ ነው። የአብሮነት፣ የይቅርታና የፍቅር ጉዞ።
ከተሞች የወትሮ ግርግራቸው ጠፍቶ ጭር በሚሉበት በዚህ የኢድ-አል አድሀ በዓል በኢንዶኔዥያ የሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ለአንድ ሳምንት ዝግ ሆነው ይቆያሉ። የግል ካምፓኒዎች ለሰራተኞቻቸው የአምስት ቀን ፍቃድ ይሰጣሉ።
በዚህ ወቅት በየቀኑ ለተወሰነ ሰዓት አገልግሎት የሚሰጡት ባንኮችና መሰል ተቋማት ብቻ ናቸው።
በምትኩ የገጠር ከተሞችና መንደሮች በጎብኝዎች ተሞልተው ይደምቃሉ።
በዚህ ሁኔታ ከበዓሉ በፊት ሁለትና ሶስት ቀናት ቀደም ብለው ከያሉበት ተሰባስበው ወደ ሀገር ቤት የገቡት የሙዲክ ተጓዦች በበዓሉ ቀን የኢድ ሰላትን በመስጂዶች ተሰባስበው ከሰገዱ፤ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የተለያዩ ምግቦችን በማዘጋጀት ከተመገቡ በኋላ፤ በየአካባቢያቸው ያሉ አዛውንቶችን መጎብኘት ይጀምራሉ፤ የተለያዩ ስጦታዎችን ያበረክታሉ፤ ከአዛውንቶች ምርቃት ይቀበላሉ እንዲሁም ከተጣሉት ይቅርታ ይጠይቃሉ።
በዚህ ሁኔታ በዓልን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለቀናት ሲያከብሩ የቆዩት የሙዲክ ተጓዦች፤ ከበዓሉ መጠናቀቅ በኋላ የተወሰኑ ቀናትን አሳልፈው ወደየመጡበት ይመለሳሉ።
በዚህ መልኩ ሲከበር የኖረው የሙዲክ ባህል በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ከመስተጓጎሉ ውጭ፤ በኢድና በአረፋ በዓል ለብዙ ዘመናት በዚህ መልኩ እየተከበረ ይገኛል ።