በ99 ዓመት ዕድሜውም ንቁ ነው፤ ተፈጥሮን ገላልጦ ለዓለም ሲያሳይ ኖሮ በዚህ ዕድሜው የተረዳውን "መቶ ዓመታት ለሚጠጋ ዕድሜ በዚህ ምድር ላይ ኖሬያለሁ፤ በዚህ ዕድሜዬ የተረዳሁት የምድራችን አስፈላጊ ነገሮች የሚገኙት በገጸ ምድር ሳይሆን በውቅያኖሶች ውስጥ ነው፤ ውቅያኖስን ማዳን ዓለምን ማዳን መሆኑን ተረድቻለሁ፤ ለእኔ ስሠራው ከኖርኩት ተፈጥሮን መሰነድ በላይ ምንም ትልቅ ነገር የለም" በማለት ይገልጻል።
ዴቪድ ፍሬድሪክ አተንቦሮ የተወለደው እ.ኤ.አ ሜይ 8 ቀን 1926 በምዕራብ ለንደን፣ ኢስሉዎርዝ ሲሆን ያደገው በሌስተር ነው። ከቤተሰቡ ሶስት ወንዶች ልጆች ሁለተኛ ልጅ ሲሆን፣ ታላቅ ወንድሙ ሪቻርድ አተንቦሮ ተዋናይ እና የፊልም ባለሙያ ነበር።
አባቱ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ሌስተር ዩኒቨርሲቲ አቅራቢያ ያደገው አተንቦሮ ዩኒቨርሲቲው ምርምር ሊያደርግባቸው በሰበሰባቸው ቅሪተ አካላት፣ ድንጋዮች እና ዱር እንስሳት የተማረከው ገና በህጻንነቱ ነበር። ይህም ለቀጣይ ሕይወቱ መነሻ ሆነው።
ዝንባሌው አሸንፎት በካምብሪጅ ክላረ ኮሌጅ የተፈጥሮ ሳይንስን በማጥናት በ1947 በጂኦሎጂ እና በሥነ እንስሳት ጥናት የመጀመሪያ ዲግሪውን አገኘ። በሮያል ባሕር ኃይል ውስጥ ለሁለት ዓመታት ብሔራዊ አገልግሎት ከሰጠ በኋላም ወደ ሚዲያው ፊቱን በማዞር የሬዲዮ ሥራ ጀመረ።

አተንቦሮ በ1952 ከቢቢሲ ጋር በመተባበር እስከ አሁን የቆየበትን በተፈጥሮ ላይ ያተኮረ ማራኪ ፕሮግራሙን ማቅረብ እና ተፈጥሮን መሰነዱን ተያያዘው።
ይህም በተፈጥሮ ዘጋቢ ፊልም ላይ ፈር ቀዳጅ ሥራ እንደሆነ ይነገርለታል። የመጀመሪያውን ትልቅ ስኬት ያገኘው እና መታወቅ የጀመረው "Zoo Quest" (1954–1963) በሚል ተከታታይ ርዕሰ ሲያቀርባቸው በነበሩት ዝግጅቶቹ ነበር።
በዚህም ላለፉት 70 ዓመታት በቢቢሲ ቴሌቪዥን ባስተላለፋቸው ማራኪ እና ተጨባጭ የተፈጥሮ ታሪኮች አማካኝነት፤ የተፈጥሮን ሳይንስ ለእያንዳንዱ ሰው ቅርብ ከማድረጉም በላይ የአስደናቂ ተፈጥሮ መገኛ የሆነችው ምድራችን ጥበቃ እንድታገኝ የሚችለውን አስተዋጽኦ ሁሉ አድርጓል።
አተንቦሮ "Life" ብሎ በሰየማቸው ተከታታይ ሥራዎቹ ከማንም በላይ ተፈጥሮን አስመልክቶናል። ከእነዚህ ተከታታይ ሥራዎቹም "Life on Earth፣ The Living Planet፣ The Trials of Life፣ The Life of Birds፣ The Blue Planet፣ Planet Earth፣ Life in Cold Blood፣ Planet Earth II፣ Our planet እና A Life on Our Planet" ይገኙበታል።
በእነዚህ ተከታታይ እና ማራኪ ዘጋቢ ፊልሞች ከማይክሮ ሌንስ እስከ ድሮን ያሉ ዘመኑ ያፈራቸውን የካሜራ ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም ተፈጥሮን ይበልጥ ቅርብ አድርጎ ከማሳየቱም በላይ፤ የሚተርክበት መንገድም በተመልካች አእምሮ ውስጥ ተቀርጸው እንዲቀሩ የሚያደርግ ነው።

የሚያቀርበው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ጥቃቅን የሚባሉትን ጉዳዮች ጭምር እየዳሰሰ መተረኩ እና ሥራውን በፍቅር መሥራቱ ደግሞ ለአቀራረቡ ተጨማሪ ውበቶች ናቸው።
ከ2000ዎቹ ወዲህ የተፈጥሮን ምንነት በካሜራው ከማቅረብ ጎን ለጎን ወደ አካባቢ ጥብቅና እያዘነበለ መጥቷል። በነዚህ ዓመታት በሠራቸው ዘጋቢ ፊልሞቹ ስለአየር ንብረት ለውጥ እና የዓለም ሙቀት መጨመር፣ የደን መጨፍጨፍ እና የሥነ-ሕይወታዊ ሀብት መጥፋት፣ የውቅያኖሶች በፕላስቲክ መበከል እና የሕዝብ ቁጥር እድገት እና የአካባቢ ጥበቃ ዘላቂነት ላይ ትኩረት ያደረጉ ሥራዎቹን አቅርቧል።
በ2020 "A Life on Our Planet" በሚል ርዕስ ያቀረበው ዘጋቢ ፊልሙ በሕይወት ዘመኑ የተመለከታቸውን የምድራችን ለውጦች ያቀረበበት ሲሆን፣ ምድራችን ላይ የተደቀነው ፈተና አሳሳቢ መሆኑን ያሳየበት ነው።
ዴቪድ አተንቦሮ በጠንካራ ሥራዎቹ በርካታ ሽልማቶችን እና ክብሮችን አግኝቷል፤ ከእነዚህም መካከል "Knighthood (1985) and Order of Merit (2005)፣ UN Champion of the Earth (2022) እና Multiple BAFTA Awards, including in black & white, color, HD, 3D, and 4K" ይገኙበታል። ለሠራቸው ሥራዎች ክብርም ነፍሳት እና እፅዋትም ‘Attenborosaurus’ ተብለው በእሱ ስም እንዲሰየሙ ተደርጓል።

ልዩ የሆነው ድምፁ እና ከተፈጥሮ ጋር ያለው ቁርኝቱ ሥራዎቹ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገሩ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
አተንቦሮ በዚሁ የሥነ-ሕይወት ሥራው ላይ መጽሐፍትንም አበርክቷል። ከመጽሐፎቹ መካከልም "Life on Earth (1979) ፣ The Private Life of Plants (1995) እና A Life on Our Planet (2020)" በብዙዎች ዘንድ የሚታወሱ ናቸው።
እንደ የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ እና የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ባሉት ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ላይ በተደጋጋሚ ስለ ምድራችን ፈተናዎች በመናገር፣ ሁሉም ቆም ብሎ እየመጣ ያለውን አደጋ እንዲያስብ አስገንዝቧል።
አተንቦሮ ዛሬም በ90ዎቹ መገባደጃ ዕድሜው እንኳን ንቁ የተፈጥሮ ተሟጋችነቱ ቀጥሏል። እርጋታው እና ለሳይንስ ያለው ዕውቀት በመላው ዓለም ለሚገኙ ሳይንቲስቶች እና የአካባቢ ጥበቃ ባለሞያዎች ከፍተኛ መነሳሳትን የፈጠረ ከመሆኑም ባሻገር ለእርሱም ታላቅ ከበሬታን አስገኝቶለታል።
ሰር ዴቪድ አተንቦሮ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ ብቻ ሳይሆን፣ የምድራችን ትዝታ ሰናጅ ነው። ሥራዎቹ ሳይንስን፣ ታሪክ ነጋሪነትን እና የሞራል ግልፅነት አዋህደው በተፈጥሮ እና በሰው ልጅ መካከል የተገነቡ ድልድዮች ናቸው።
በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የአካባቢ ቀውስ እየተባባሰ በሄደበት በአሁኑ ወቅት ድምፁ ከተስፋ፣ ጥበብ እና ማሳሳቢያ ጋር ጎልቶ አየተሰማ ነው።
በለሚ ታደሰ