በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፉ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ ለውጥ እና እድገት እያስመዘገበ ቢሆንም ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ግንባታ ባሻገር በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን በርካታ ስራዎች እንደሚቀሩት ይነሳል።
የባንክ ዘርፉ ለውጭ ባለሐብቶች ክፍት መደረጉን አስመልክቶ ኢቲቪ የዘርፉን ባለሙያ አነጋግሯል።
በአፍሪካ ልማት ባንክ የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ሃገራት ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም በዓለም ባንክ የምስራቅና ሰሜን አፍሪካ ሃገራት አማካሪ ሆነው አገልግለዋል፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በአትላንቲክ ካውንስል የአፍሪካ ማዕከል ከፍተኛ ተመራማሪ ናቸው ገብርኤል ንጋቱ።
ባለሙያው ገብርኤል ንጋቱ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የባንኩ ዘርፍ ለውጭ ባለሐብቶች ክፍት መደረጉ የሀገር ውስጥ ባንኮች በመዋሀድ አቅማቸውን እንዲያጠናክሩና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።
የውጭ ባንኮቹ ወደ ሃገር መግባት የእውቀት ሽግግር፣ የቴክኖሎጂ እድገት፣ የአስተዳደር እና ሌሎች ልምዶችን በመጋራት የሃገር በቀል ባንኮች ለደንበኞቻቸው የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ያደርጋቸዋል ሲሉ ገልጸዋል።
ባንኮቹ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ መዋቅር ውስጥ እንዲታቀፉም ያግዛል ነው ያሉት።
ሃገር በቀል ባንኮች የውጭ ባንኮች ኢትዮጵያ ከመግባታቸው በፊት የአሰራርና መዋቅራዊ ለውጥ ማድረግ እንደሚገባቸው ነው ባለሙያው የሚያስገነዝቡት።
በዚህም ባንኮቹ የሳይበር ደህንነትታቸውን ማጠናከር፣ የብድር አገልግሎት ላይ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ጥናት በማድረግ የዋጋ እና የወለድ መጠናችውን ማስተካከል፣ ከደንበኞች ጋር ባላችው ግንኙነት ደንበኖች ወደ ባንኩ ሳይሆን ባንኩ ወደ ተጠቃሚዎች መሄድ ይኖርበታል ብለዋል።
የደንበኞችን ፍላጎት በማሟላት ረገድ ፈጣን እና ዘመናዊ አገልግሎት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ግለሰባዊ አገልግሎትና ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ አሰራር በመፍጠር የኢንቨስትመንት አገልግሎት ላይ መስራት ይገባል ነው ያሉት።
አያይዘውም የዲጂታል ባንኪንግ ቴክኖሎጂን የበለጠ በማጠናከር ዘመናዊ የባንክ አገልግሎትን ማስፋፋት መሰረታዊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የውጭ ባንኮች ወደ ሃገር ውስጥ መግባት ለሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለውም አስረድተዋል።
የውጭ ባለሐብቶቹ አዲስ ካፒታል ይዘው ወደ ሃገር ውስጥ ስለሚቀላቀሉ ለመሰረተ ልማት ግንባታ እንዲሁም የኢንደስትሪ ፕሮጀክቶች ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ይረዳል ብለዋል ባለሙያው።
ከዚህ ቀደም ያልታቀፉ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር በመፍጠርም ጥቃቅን እና አነስተኛ ድርጅቶች የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ የፋይናንስ አቅማቸው እንዲጎለብት ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል።