በአንድ ሰውነት ብዙ ማንነት ምንድን ነው?

1 Day Ago 463
በአንድ ሰውነት ብዙ ማንነት ምንድን ነው?

የሰው ልጅ ጤና በርካታ መልኮች አሉት፤ አንድ ሰው ጤነኛ ነው ለመባል በሰውነት፣ በአዕምሮ እንዲሁም በማኅበራዊ ሕይወቱ ጤናማ የሆነ ግንኙነት ሊኖረው ይገባል።

ከአዕምሮ ጤና ጋር በተያያዘ በርካታ የሕመም ዓይነቶች እንዳሉ ባለሙያዎች ሳይንሳዊ መረጃዎችን አስደግፈው ይገልጻሉ።

አንዳንዶቹ ታዲያ ያልተለመዱ ዓይነት ከመሆናቸውም ባሻገር በትክክል በሽታ ስለመሆናቸው እንኳን ለማመን የሚያስቸግሩ ዓይነት ሆነው እናገኛቸዋለን። 

እንዲህ ናቸው ተብለው ለማስረዳት ከሚያስቸግሩ የአዕምሮ የጤና ችግሮች መካከል አንዱ የሆነውን ‘ደባል ስብዕና’ ወይም ብዙ ስብዕና (Multiple Personality) ወይም በአሁኑ አጠራሩ Multiple Personality Disorder [DID] የተሰኘውን የሕመም ዓይነት ምንነት፣ መንሥኤዎቹን፣ የበሽታውን ዓይነት፣ ምልክቶቹን እንዲሁም የሕክምና ሂደቱን እንመለከታለን።

በተፈጥሮ ሁሉም ሰው የተወሰነ ያህል በሕይወቱ ለሚፈጠሩ ከባድ ነገሮች ምላሽ የሚሰጥበት መንገድ አለ። ሁሉም ሰው ለመቀበል ከባድ የሆነ ክስተት ሲያጋጥመው ለዛ ነገር ምላሽ የሚሰጠው በተለያየ መንገድ ሊሆን ይችላል።

በመጮህ፣ በማልቀስ፣ ያንን ሕመም ለሌላ ሰው በማካፈል፣ በብቸኝነት፣ የተለያዩ የእምነት ቦታዎች በመሔድ ወይም ያንን የተፈጠረውን ነገር ለመቀበል ለራስ ጊዜ በመስጠት እና በሌሎች መንገዶች ምላሽ ሊሰጥ ይችላል።

አንዳንድ ከባድ የሆኑ ነገሮችን ለመቀበል የራሱ የሆነ ያህል ጊዜ ቢወስድም ነገር ግን አንዳንዴ ምንም ያህል ጊዜ ብንወስድ ፈፅሞ አዕምሮአችን ሊቀበለው የማይችለው ነገር በሕይወታችን ያጋጥመናል። የእኛ ማንነት እና የተፈጠረው ነገር የሚፈጥርብን ስሜት ሲጋጭ አዕምሮአችን ከእኛ እውቅና ውጪ በሆነ መንገድ አፀፋ ይመልሳል።

ማነታችን ለሁለት ይከፈላል፤ ይህ ሁኔታ በብዙ አድጎ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ብዙ ስብዕና ያለውን ሰው በአዕምሮአችን ይፈጥራል።

ብዙ ስብዕና ያለው ሰው ስንል በአንድ ሰው ሰውነት ውስጥ ከዛ ሰው እውቅና ውጪ በሆነ መንገድ ውስጡ የሌላን ሰው ማንነት ሲላበስ ወይም ወደ ሌላ ሰው የመቀየር እንዲሁም የሁለት እና ከዚያ በላይ ሰዎችን ማንነት ሲያንፀባርቅ ማለት እንደሆነ የጤና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

በእንደዚህ ያለ የአዕምሮ ሕመም ውስጥ የሚገኙ ሰዎች እጅግ አልፎ አልፎ ብቻ የሆነ አካል ውስጣቸው እንዳለ ሊሰማቸው ይችላል እንጂ አብዛኛው ጊዜ በውስጣቸው ስላሉት አካላት ከነመፈጠራቸውም አያውቁም።

በመሆኑም ሙሉ ለሙሉ በእነርሱ ቁጥጥር ስር ሲሆኑ አካቸው ላይ የመቁሰል ወይም ከሌላ ሰው ጋር የመጋጨት ነገር ተፈጥሮ ወደ ማንነታቸው ሲመለሱ ምን መሆናቸውን ሲጠየቁ ስላደረጉት ነገር ምንም አያስታውሱም ወይም ያደረጉትን ነገር አያውቁም ማለት ነው።

ለዚህ የበሽታ ዓይነት ተጋላጭ ከሚያደርጉ ነገሮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሱት ውጥረት የሚፈጥሩ አጋጣሚዎች እና የሥነ-ልቦና ቀውሶች፦ ለምሳሌ ያህል በልጅነት የሚደርሱ ከባድ በደሎች፣ በጣም ዘግናኝ ፆታዊ ጥቃቶች፣ በሕይወት የሚያጋጥም ከባድ ኀዘን በዚህ ሕመም ተጋላጭ በሆኑ ታካሚዎች ላይ ከሚስተዋሉ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። 

በአስተዳደግ ላይ የሚፈጠር በደል ልጆችን ለከባድ የስብዕና ቀውስ የሚያጋልጣቸው በመሆኑ ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ በመግባት የሥነ-ልቦና አፀፋዊ ምላሽ ማሳየት ይጀምራሉ፤ ወይም ከእነርሱ ጋር ቁርኝት ያለውን ሰው ማጣት ለእንደዚህ ያለ ሕመም ሊያጋልጣቸው ይችላል።

አዕምሮ ላይ የሚፈጠር ጫና የተፈጠረውን ነገር አዕምሮ ለመቀበል ሲቸገር እና አዕምሮ ለሁለት ሲከፈል ለዛ ጉዳይ አዕምሮ የሚሰጠው አፀፋዊ ምላሽ ነው።

በቀላሉ በዚህ የሕመም ዓይነት ዙሪያ በሀገራችን ከተሰሩ ፊልች መካከል “ማን ያዘዋል” የተሰኘውን ፊልምን መጥቀስ እንችላለን፤ ከውጭ ፊልሞች ደግሞ SPLIT የተሰኘው ፊልም ይጠቀሳል። 

TELL ME YOUR DREAMS (ሕልምሸን አጫውቺኝ) በሚል ወደ አማርኛ የተተረጎመው የሲድኒ ሼልደን መፅሀፋ ለዚህ የሕመም ዓይነት ጥሩ ማጣቀሻ ሆኖ መቅረብ ይችላል።

ይህ የሕመም ዓይነት ምልክቶቹን ለመለየት በጣም አስቸጋሪ ከሆኑ የሥነ-ልቦና ቀውስ ዓይነቶች መካከል አንዱ ቢሆንም ከምልክቶቹ አንዱ አንድ ሰው ከሆነ ቦታ ወደ ሆነ ቦታ ሄዶ እዛ ቦታ ላይ እንዴት እንደተገኘ እንዲሁም ምን ማድረጉን ምንም የማያስታውስ ከሆነ ወይም የሚያስታውሰው የሆነ ዓመት ላይ ያለውን ትውስታ ብቻ ከሆነ፣ ከዛን ጊዜ በኋላ የኖረውን ሕይወት የማያስታውስ ከሆነ እና በተደጋሚም እንደዚህ ዓይነት ነገሮች የሚስተዋሉበት ከሆነ የበሽታው አንዱ ምልክት ሊሆን እንደሚችል የሥነ-ልቦና አማካሪ ዶክተር አስራት ለኢቢሲ ዶትስትሪም ገልጸዋል።

የሳይኮሎጂ ባለሙያዋ ዶክተር ዲና ሲሳይ እንደነገሩን ከሆነ፣ ትክክለኛው የበሽታው የተጠቂው ማንነት ‘ሆስት’ ይባላል፤ በውስጡ የሚፈጠሩት ማንነቶች ደግሞ ‘አርተር’ ይባላሉ።

ይህም በሕይወታችን የተፈጠረውን መቀበል የከበደንን ነገር የሚያስታውስ አንዳች ነገር ሲፈጠር፣ ለምሳሌ ጉዳት ያስተናገድንባቸው ቦታዎች ስንሄድ ወይም ያንን የሚያስታውስ ሽታ ሲሸተን ከውስጥ የተደበቁ ማንነቶች ለክስተቱ ምላሽ ለመስጠት እራሳቸውን ማንፀባረቅ ይጀምራሉ።

በዚህ ወቅት ‘አርተር’ ሊሚያሳየው ማንኛውም ባህሪ ጉዳቱን የሚያስተናግደው ወደ ማነቱ ሲመለስ የሰውየው ትክክለኛ ማንነት ወይም ሆስት ነው ማለት ነው።

ከሰው ጋር አላስፈላጊ ግጭት ውስጥ ገብቶ የተለያዩ ጉዳቶች በሰውነቱ ላይ ተፈጥረውበት ሊሆን ይችላል ወይም የተለያዩ ወንጀሎችንም ፈፅሞ በሌላ አካል ላይ ጉዳት ሊያደርስም ይችላል።

ጉዳዩን ከባድ የሚያደርገው ነገር ደግሞ በገዛ ሰውነቱ ከአዕምሮ እውቅና ውጪ የሚደረግ ነገር በመሆኑ ወደ ማንነቱ ሲመለስ የሆነውን አንዳችም ማስታወስ አለመቻሉ ነው።

ይህ ‘አርተር’ የሚባለው ሌላው ማንነት ከትክክለኛው ሰው ስብዕና ጋር ፍፁም ተቃራኒ የሆነ ባህሪይ ወይም ሌላ ፆታ አሊያም በዕድሜ እጅግ የተራራቀ ልዩነት ያለው ሊሆን ከመቻሉም በላይ ከትክክለኛው ሰው ጋር የሚወዱት እና የሚጠሉት ነገሮች ሳይቀር እጅግ የተለያየ እና ተቃራኒ ሊሆን ይችላል።

ይህንን የሕመም ዓይነት እጅግ የሚገርም ነው እንድንል ከሚያስገድዱን ነገሮች መካከል በ‘ሆስት’ ላይ ያሉ ሌሎች የሕመም ዓይነቶች ለምሳሌ እንደ አላርጂክ እና የመሳሰሉት ነገሮች ‘አርተር’ ሲጠቀማቸው ምንም ዓይነት የሕመም ስሜት የማይንፀባረቅበት መሆኑ ነው ይላሉ ባለሙያዋ።

 

ሕክምናውስ?

የጥምር ስብዕና ወይም ብዙ ስብዕና ሕመም ሕክምና በመጀመሪያ የተፈጠረውን ነገር ምነቱን ከማጣራት እንደሚጀምር የጤና ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

ጉዳዩን ክትትል የሚያደርገው ሳይካትሪስት ወይም ክሊኒካል ነርስ ሌላ ተያያዥ ጉዳቶች መኖር አለመኖሩን ያጣራል። ውስጡ ሌላ ጭንቀት ሊኖር ስለሚችል መድኃኒት መውሰድ ካለበት እርሱን ማስተካከል የመጀመሪያው ተግባር እንደሆነም ይመክራሉ።

ለዚህ ሕመም ሳይካትሪስቶች እና ሳይኮሎጂስቶች በጋራ በመሆን ሕክምናውን የሚሰጡ ሲሆን በሀገራችንም በተለያዩ የመንግስትም ሆነ የግል የአዕምሮ ሕክምና መስጫ ተቋማት ውስጥ ተኝቶ መታከምን ጨምሮ አገልግሎት እንደሚሰጥ የሳይኮሎጂ ባለሙያዋ ዶክተር ዲና ሲሳይ ትገልጻለች።

የሁሉም ሰው ሥነ-ልቦና የሚዋቀረው ከቤተሰብ፣ ከአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ከሃይማኖት ተቋማት እንደመሆኑ መጠን በሀገራችን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ማኅበረሰቡ በተለያየ ጊዜ ለሚያጋጥመው ፈተና መፍትሔ ማግኛ አንዱ መንገድ የሃይማታዊ ተቋማት ናቸው።

ሳይንሱ ትንሽ ያራቀቀውን ነገር ማኅበረሰቡ በሚያምንበት እና በራሱ መንገድ መፍትሔ ለማግኘት ይሞክራል። ይህ እንደመሆኑ መጠን በርካታ ይህን እና መሰል በአዕምሮ መታወኮች የተጠቁ ሰዎች ወደ እምነት ተቋማት በመሔድ መፍትሔ እንደሚያገኙ የዘርፉ ባለሙዎች ያረጋግጣሉ።

ይህ በዚህ እንዳለ አንዳንድ የአዕምሮ ሕመሞች ግን የግድ የባለሙያ እገዛ የሚፈልጉ በመሆናቸው ማኅበረሰቡ ይህንን ተገንዝቦ ወደ ሕክና ተቋማት በመሔድ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኝ ባለሙያዎች ይመክራሉ።

በኔፍታሌም እንግዳወርቅ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top