ማየትም መስማትም አለመቻል ያልገደባት ጀግና - ሔለን ኬለር

2 Days Ago 324
ማየትም መስማትም አለመቻል ያልገደባት ጀግና - ሔለን ኬለር

ሔለን ኬለር ሕይወት በጣም ከፍተኛ ከሆኑት የፅናት፣ ቆራጥነት እና የትምህርት የለውጥ ኃይል ታሪኮች ለብዙዎች እንደ ምሳሌ ሆኖ የሚታወስ ነው።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሰኔ 27 በ1880 በአሜሪካ፣ አላባማ ግዛት በቱስኩምቢያ ከተማ የተወለደችው ኬለር በተወለደች በ19 ወሯ ነበር በደረሰባት ሕመም ምክንያት የማየት እና የመስማት ችሎታዋን ያጣችው።

ታዲያ ወሳኝ የሆኑ የስሜት ሕዋሳቶቿን በልጅነቷ ያጣችው ሔለን ኬለር፣ በብዙ የሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ በማለፍ እንደ መስማት እና አለማየት የመሳሰሉ የአካል ውስንነቶች የአንድን ሰው አቅም ማደግ እና ስኬታማ መሆንን እንደማይገድቡ ትምህርትን በሚገባ በመማር አቅሟን ማሳየት የቻለች ናት።

በዓለም ታዋቂ ደራሲ፣ አክቲቪስት እና ጠበቃ የሆነችው ሔለን ኬለር፣ ከልጅነቷ ጊዜ ጀምሮ አዕምሯዋ ብሩህ እንደነበር እና ከሰዎች ጋር በቋንቋ መግባባት ባለመቻሏ በጣም ትበሳጭ እንደነበር ይነገራል።

በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል ላይ የምትገኘው አን ሱሊቫን የተባለች መምህርት ከፐርኪንስ ዐይነ ሥውራን ትምህርት ቤት ወደ ሔለን ኬለር የሕይወት ጉዞ ውስጥ ገባች፤ ከዛን ጊዜ ጀምሮ የሔለን ሕይወት ተለወጠ።

አን ሱሊቫን ሔለን ኬለርን ቋንቋን ለማስተማር ቃላቶችን በእጇ በመጻፍ ታስተዋውቃት የነበረ ሲሆን ለምሳሌ፣ "ውኃ" የሚለውን ቃል በእጇ ላይ ከሚፈሰው ቀዝቃዛ ፈሳሽ ጋር በማያያዝ እጇ ላይ የውኃ ምልክት ታደርግ ነበር።

የሔለንን ሕይወት ለማስመር የምትተጋው አን ሱሊቫን ከሔለን ጎን በመሆን ብሬይልን አስተማረቻት፤ ቀስ በቀስም ሔለን በምልክት ቋንቋ መናገርን ተማረች። በመቀጠልም በፐርኪንስ ዐይነ ሥውራን ትምህርት ቤትና ራይት-ሁማሰን ተብሎ በሚጠራ መስማት ለተሳናቸው ትምህርት ቤት ገብታ መማር ጀመረች።

በመጨረሻም ራድክሊፍ ኮሌጅን ጨምሮ በተለያዩ ተቋማት ገብታ ከፍተኛ ትምህርትዋን በመማር፤ እ.ኤ.አ በ1904 ዓ.ም ከኮሌጅ በማዕረግ ተመረቀች። ይህ የእሷ የግል ድል ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአካል ጉዳተኞች ታላቅ ስኬት ሆኖ ኖሯል።

ሔለን ኬለር ብዙዎችን ያስደነቀ የሕይወት ታሪኳን ፅፋ ሚሊዮኖችን  አነሳስቷል፤ ከ40 ዓመታት በላይም  በአሜሪካ ፋውንዴሽን ለአካል ጉዳተኞች  ጠበቃ በመሆን ሰርታለች።

ለሴቶች ምርጫ፣ ለሰራተኛ መብቶች፣ ለፍትሕ በመስራት የምትታወቀው ሔለን ኬለር እ.ኤ.አ በ1920 የአሜሪካ ሲቪል ነፃነቶች ሕብረትን በመመስረት ከሶሻሊስት ፓርቲ ጋር ትሰራ ነበር።

ሔለን ኬለር በታሪክ ውስጥ በጣም ታዋቂዋ መስማት እና ማየት የተሳናት ሰው ስትሆን፤ አርቲስቶች፣ አስተማሪዎች፣ የመብት ተሟጋቾች እና ሌሎች ባለሞያዎች በተለያዩ እንከኖች እያለፉ የሷን የሕይወት ተሞክሮ ተምሳሌት በማድረግ አካል ጉዳተኝነት የሰውን ልጅ  አቅም እንደማይገድብ ማሳያ እየሆኑ ነው።

ሔለን ኬለር በአንድ ወቅት “ከዓይነ ስውርነት የሚከፋው ማየት አለመቻል ሳይሆን አይቶም ራዕይ ማጣት ነው" ብላ ነበር። ሕይወቷ የተግባር ጥሪ የሆነው ሔለን በዓላማ የኖረች፤ በድፍረት ለሌሎች የተሟገተች ሕይወትን አካታች በማድረግ ትምህርት ለሁሉም እንዲስፋፋ እንዲሁም ዓለምን ለሁሉም ምቹ ቦታ ማድረግ እንደሚገባ አስተምራለች።

ሔለን ኬለር “ዓይኖቻቸው በብርሃን ከተሞሉ ነገር ግን ምንም ከማያዩ ሰዎች ጋር ሄጃለሁ” በማለት ሰዎች ሩህሩህ እንዲሆኑ ፤ የተለያየ ችሎታ ያላቸውን እንዲያደንቁ እና በደንብ እንዲረዷቸው ትመክራለች።

ሔለን ግብዋን በግልጽ በማስቀመጥ በእቅድ ትመራ የነበረ ሲሆን ታሪኳ የመግባባት ክህሎትን ለማሳደግና ለመማር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ማሳያ መሆኑንብዙዎች ይመሰክራሉ።

የሔለን ኬለር ስኬቶቿ ጥራት ያለው ትምህርት በማግኘት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ሁሉም ሰው  አካል ጉዳተኛም ሆነ ጉዳት የሌለበት፤ በትክክለኛው ድጋፍ የመማር እና የማደግ አቅም እንዳለው ያረጋገጠ ነበር።

የቆራጥዋ ሔለን ኬለር ስኬት ሲነሳ  የአን ሱሊቫን የማይናወጥ ድጋፍ እና አሳዳጊ ቤተሰቦቿ ጉልህ ሚና  የእርሷን የሕይወት ጉዞ ጥንካሬ የጀርባ አጥንት እንደሆኑ ይነሳል።

ሔለን ኬለር ያገኘችውን መድረክ ሁሉ በመጠቀም አካል ጉዳተኞች እንዳይገለሉ ተናገራለች። የሔለን ኬለር አርዓያነት ሁሉንም ችግሮች በመቋቋም ድምፅ በማሰማት እና ዕድሎችን በመጠቀም የበለጠ ፍትሐዊ እና ሁሉን አቀፍ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ምሳሌ የሚሆን ነው።

በሔለን ተስፋዬ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top