ከአልጎርዚም ቅኝ ግዛት መጠንቀቅ ያለባት አፍሪካ

4 Days Ago 435
ከአልጎርዚም ቅኝ ግዛት መጠንቀቅ ያለባት አፍሪካ

ዓለም አሁን በሚገኝበት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘመን ሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) በሚያስደንቅ ፍጥነት ለውጦችን እያስመዘገበ ይገኛል።

እ.አ.አ በ1950ዎቹ እንደተጀመረ የሚነገረው ቴክኖሎጂው ለእለት ተእለት የሰው ልጆችን ችግር መፍታት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ውጤት እየሆነ መጥቷል።

ቴክኖሎጂው እድሜን እስከመቀጠል እና የምግብ ዋስትናን እስከማረጋገጥ የደረሰ ሲሆን፣ የዕለት ተዕለት ህይወትን እያቀለለ ስለመምጣቱም ይነገራል።

ኢትዮጵያም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በ2012 ዓ.ም የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አቋቁማለች። ኢትዮጵያ ትኩረት አድርጋ የምትሠራው ሀገር በቀል የሆኑ እና ለተጠቃሚው እንግዳ ያልሆነ ሰው ሠራሽ አስተውሎት አበልጽጋ ጥቅም ላይ እያዋለች ትገኛለች።

በ38ኛ የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ይህን አስመልክተው ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣ ቀጣዩ ዘመን የዲጂታል ቴክኖሎጂ በተለይም አርተፊሻል ኢንተለጀንስ መሆኑን እና ኢትዮጵያም ሆነች አፍሪካ በዘርፉ ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቅሰዋል።

ሰው ሠራሽ አስተውሎቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎቹ እንዳሉት ሁሉ በርካታ ስጋቶች እና አሳሳቢ ነገሮችም አሉት። ከሥነምግባር አንፃር ከሰዋዊነት ያፈነገጡ ነገሮች ሊፈጠሩ መቻላቸው፣ አልጎሪዝሙ የተዛባ እና አድሎአዊነት የበዛበት መሆኑ፣ ከሰው ልጆች ባህል እና እሴት ያፈነገጡ ክስተቶች ሊኖሩበት መቻላቸው ከአሳሳቢ ጎኑ መካከል ናቸው።

ሰው ሠራሽ አስተውሎት የሰውን ልጅ እየተኩ መሆናቸውም ሰዎችን ሥራ አጥ ሊያደርጋችው ይችላል የሚል ፍርሃት ሌላው የዘርፉ አሳሳቢ ጎን ነው። አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ወደ ትክክለኛነት የተጠጋ ስለሆነ ትክክለኛ የሚመስሉ ነገር ግን አሳሳች መረጃዎችን በመፈብረክ በሰውልጆች ዘንድ ከባድ ስጋት ደቅኗል።

አርተፊሻል ኢንተለጀንስ የደቀነውን ስጋት ለመወጣት ኢትዮጵያ ምን ማድረግ አለባት?

በዚህ ጉዳይ የተለያዩ የዘርፉ ባለሙያዎች አስተያየቶችን ይሰጣሉ። ከእነዚህም ባለሙያዎች መካከል ኢትዮጵያዊቷ አበባ ብርሀኔ (ፒኤችዲ) በሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ የሠራችው ጥናታዊ ጽሑፍ የሚጠቀስ ነው። ባለሙያዋ እንደምትለው የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ አልጎሪዝም በኮድ ውስጥ የታቀፈ ዘረኝነት እና በሴቶች ላይ የተዛባ አመለካከት ያለው ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ከትውልደ ሕንዳዊው ፕሮፌሰር ሰር ቪኔ ፕራህቡ ጋር በመሆን ተጨባጭ ጥናት ሠርታለች።

ጥናታዊ ጽሑፋቸው ሰው ሠራሽ አስተውሎት በአልጎሪዝሙ ውስጥ በኮድ አማካኝነት የተጫኑ ፕሮግራሞች ዘረኝነትን የሚያንፀባርቁ መሆናቸውን የሚያመላክት ስለመሆኑ ጠቅሰዋል። በተጨማሪም ሠው ሠራሽ አስተውሎት ባለው የተዛባ አመለካከት ምክንያት በእድሜ የገፉ ሠራተኞች፤ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ማኅበረሰቦች፤ ስደተኞችን እና ልጆችን በአሉታዊ መልኩ እንደሳሏቸው በጥናታዊ ጽሁፋቸው አመላክተዋል። ኮዱ የሚፈጠረው በነጭ ወንዶች እንደሆነ የምትገልፀው አበባ ብርሀኔ (ፒኤችዲ) አብዛኛውን ጊዜ ነጭ ላልሆኑ እና ለሴቶች የሚታይ ጥላቻ እንደሚንፀባረቅበት ጠቅሳለች። በቀሪው ዓለም ላይ ያለው ተፅዕኖ ከባድ በመሆኑ ይህንን ለመታገል መወሰኗን ገልጻ በተደራጀ አጀንዳዎች ተፈጥሯል ስለምትለው "Algorithmic colonization" በስፋት ተንትናለች።

የኮምፒውተር ሳይንስን ከቅኝ ግዛት ነፃ አስተሳሰብ እንዲኖረው ለማድረግ በመሥራት ላይም ትገኛልች።

ለአፍሪካም የሚያስፈልጋት እነዚህን ጉዳዮች ነቅሳ በማውጣት የራሷን መንገድ መከተል ነው የምትለው ባለሙያዋ፣ በግድ የለሽነት እኛን የማይመስሉ እንዲሁም ከማኅበረሰቡ እሴት ባህል እና ስነምግባር ጋር አብረው የማይሄዱ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለመጠቀም መፍቀድ ወደፊት በትውልድ ላይ ማኅበራዊም ሆነ ሥነ-ልቦናዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል ታነሣለች።

እንደ መፍትሔ ሐሳብ የሚነሣው በአፍሪካውያን በራሳቸው የተሠራ እና ለአፍሪካ የሚሠራ፣ ለአፍሪካ ማኅበረሰብ ችግር መፍትሔ የሚሰጡ አልጎሪዝሞችንን መፍጠር አስፈላጊ እንደሆነ ይገለጻል።

አፍሪካ ቴክኖሎጂው ለሀገር ዕድገት የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ያህል የከፋም ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ተገንዝባ በበጎ ጎኑ በመጠቀም የሚያስችል ሕግ እና ሥርዓት እንዲሁም ባህል እና እሴትን በማይጥስ መልኩ ሥራ ላይ እንዲውል ጥብቅ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ ልትከተል እንደሚገባ የዘርፉ ተመራማሪ አፍሪካውያን ምክረ-ሐሳብ ነው።

በኔፍታሌም እንግዳወርቅ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top