ሀጅ ከአምስቱ የእስልምና እምነት መሰረታዊ ምሶሶዎች አንዱ ሲሆን ምዕመናን በሕይወት ዘመናቸው የኢኮኖሚያዊ አቅማቸው ሲፈቅድ ሊያከናውኑት የሚገባ ሐይማኖታዊ ግዴታ መሆኑ ይገለጻል፡፡
ሙስሊም የሆነ ጤናማ ሰው ሁሉ በሕይወት ዘመኑ ቢያንስ አንድ ጊዜ ሀጅ ማድረግ ሐይማኖታዊ ግዴታውም ነው፡፡
ሀጅ ለማድረግ አቅማቸው በእርጅና ምክንያት የማይፈቅድላቸው እናትና አባቶች በወጣቶች ታግዘው የሚያከናውኑት ሐይማኖታዊ ተግባር መሆኑ ይነገራል፡፡
እንደሐይማኖቱ አስትምህሮ፤ ሀጅ በመካ ካዕባን 7 ጊዜ ከመዞር ይጀምራል። ወደ ሚና ይሻገራል፣ አረፋት ተራራ በጠዋት ይወጣል እስከ ማታም ይዘልቃል፣ ወደ ሙዝደልፋ ላይ ይኬዳል፤ ፀሎታዊ ስርዓቱም ይቀጥላል፡፡
ሚና ከመካ 7 ኪሎ ሜትር ርቀት ያለው ሐይማኖታዊ ስፍራ ነው፡፡ በዚህ ቅዱስ ስፍራ የሀጅ ስነ-ስርዓቱን ለሚያከናውኑ ሀጃጆች ማረፊያ እንዲሆን ተደርጎ የተዘጋጀ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ድንኳን የተዘጋጀበት ከተማ ነው፡፡
አረፋ ደግሞ ከመካ 15 ኪሎ ሜትር ይርቃል፡፡ በዚህ ቅዱስ ስፍራ ምዕመናን በጠዋት ወጥተው ዱዓቸውን ለፈጣሪያቸው አሏህ አድርሰው ማምሻውን ወደ ሙዝደልፋ ይመለሳሉ፡፡
ይህ ቀን የዙልሂጃ 9ኛው ቀን በመሆኑ በርካቶች በጾምና በፀሎት ያሳልፉታል፡፡
በሙዝደልፋ ሀጃጆች ዱዓ ያደርጋሉ፤እረፍት ይወስዳሉ፡፡ በዚህ እለት የሚወረወረውን ድንጋይ ይለቅማሉ፡፡
ወደ ሚና በመመለስም 7 ጊዜ የለቀሙትን ድንጋይ ወደ ገደሉ ይወረውራሉ።
በእስልምና አስተምሮ ነቢዩ ኢብራሂም ልጃቸውን እስማእልን ለአረፋ እንዲሰውት ፈጣሪ አዟቸው ወደ አረፋት ሲወስዱት ሰይጣን እንዴት አንድ ያለህን ልጅህን ትሰዋለህ እያለ ሲወተውታቸው እምብኝ ብለው የፈጣሪ አሏህን ትእዛዝ ያከበሩበት ቦታ ነው፡፡
ይህንን የመታዘዝ ተግባር ለማስታወስ ምዕመናን ድንጋይ በመወርወር ያከብራሉ፡፡
የዘንድሮን የሀጅ ስነ-ስርዓት የተሳለጠ ለማድረግም የሳዑዲ ዓረቢያ ትራንስፖርትና ሎጂስትክስ ሚኒስቴር ከ25ሺ በላይ ባሶችን፣ 9ሺ ታክሲዎችን የባቡር ትራንስፖርቶችን ማቀናጀቱን የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የሳዑዲ ዓረቢያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ከ1.8 ሚሊዮን ሀጃጆችን ከተለያዩ ሀገራት ለማመላለስ 2000 በረረዎችን በማድረግ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሀጃጆችን ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ እንደሚያደርስ ሚኒስቴሩ ያወጣው መረጃ ያመልክታል፡፡
በአጠቃላይ ከ18 ሺ በላይ አስተናጋጆች ያለውን ሁኔታ ቅኝት የሚደርጉበት፣ሀጃጆች መንገድ ስተው ሲያገኙ የሚጠቁሙ፣ የታመመውን ወደ ሆስፒታል የሚወስዱ፣ የትራንስፖርት ሂደቱን የሚያቀናጁት፣ ማረፊያ ሆቴሎችን በማሳየት ምዕመናን የሀጅ ስርዓቱን ጠብቀው እንዲከውኑ የሚረዱበት ሁነት ቀድሞ ዝግጅት የተደረገበት ነው፡፡
መካ፣ ሚና፣ አረፋ እና ሙዝደሊፋን የሚያገናኙ ፈጣን ባቡሮችና የትራንስፖርት መስመሮችም ሚሊዮኖችን ያስተናግዳሉ።
የዘንድሮውን የሀጅ ስነ-ስርዓት የተሳለጠ ለማድረግና ሊደርስ የሚችል ማንኛውንም አደጋ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እንዲያስችልም የአየር፣ የምድርና የሞተር ትራንስፖርት አገልግሎት በተሟላ መንገድ መዘጋጀቱን የሳዑዲ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ 43ሺህ ሀጃጆች በሀጅ ስነ ስርዓቱ ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ከሳዑዲ ዓረቢያ የሀጅና ኡምራ ሚኒስቴር ኮታ የተፈቀደላት ሲሆን፤ ከ6 ሺህ 200 በላይ የሚሆኑት መሳተፋቸውን ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በመሀመድ ፊጣሞ
#EBC #Ebcdotstream #መካ #መዲና #አረፋ