ለአርሰናል ቤንጃሚን ሼሽኮ ወይንስ ቪክቶር ጊዮኬሬሽ?

1 Day Ago 606
ለአርሰናል ቤንጃሚን ሼሽኮ ወይንስ ቪክቶር ጊዮኬሬሽ?
ደጋፊዎቹን ብቻ ሳይሆን የክለቡን ሃላፊዎች ጭምር ለሁለት የከፈለው የሼሽኮ እና ጊዮኬሬሽ ዝውውር አርሰናል ለ3ኛ ተከታታይ አመት 2ኛ ደረጃን ይዞ ከማጠናቀቅ ያለፈ ዋንጫ እንዳያነሳ ካደረጉት አንደኛው ምክንያት የአጥቂ ችግር ነው፡፡
 
የውድድር አመቱ ከመጠናቀቁ ተጫዋች ለማስፈረም እንቅስቃሴ የጀመረው አርሰናል በዋናነት ከሁለት አጥቂዎች ጋር ስሙ ተያይዟል፡፡
 
ቤንጃሚን ሼሽኮ እና ቪክቶር ጊዮኬሬሽ።
 
ሁለቱም አጥቂዎች በተጠናቀቀው የውድድር አመት ከክለቦቻው ጋር የተሳካ ጊዜ አሳልፈዋል፡፡
 
ስሎቬንያዊው ሼሽኮ 21 ግቦችን ሲያስቆጥር ስዊዲናዊው ጊዮኬሬሽ በዚህ አመት ብቻ 54 ግቦችን በስሙ አስመዝግቧል፡፡
 
የአርሰናል አዲሱ ስፖርቲንግ ዳይሬክተር አንድሪያ ቤርታ እና ሚካኤል አርቴታ ቡድኑ ሁነኛ አጥቂ እደሚያስፈልገው ልዩነት ባይኖራቸውም የትኛው ተጫዋች ይሁን የሚለው ላይ ግን ገና ስምምነት ላይ አልደረሱም።
 
የዘ አትሌቲኩ ጸሃፊ ዳን ሸልደን የእግር ኳስ ወኪሎችን፣ የስፖርቲግ ዳይሬክተሮችን እና አሰልጣኞች አናግሮ ባሰፈረው ጽሁፍ ላይ መድፈኞቹ ወደ የትኛው አጥቂ ሊያመዝኑ እደሚችሉ አስቀምጧል፡፡
 
አንድ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ አሰልጣኝ አርሰናል ያለበትን ችግር መቅረፍ ከፈለገ ማስፈረም ያለበት የ21 አመቱን ቤንጃሚን ሼሽኮን ነው ይላል፡፡
 
ተጫዋቹ ወጣት እንደመሆኑ መጠን አርቴታ በሚፈልገው መንገድ ለመስራት የሚያመቸው ሲሆን በተለይ ደግሞ ፍጥነቱ እና ከኳስ ጋር ያለው ቅርበት ተመራጭ እንደሚያደርገው አሰልጣኙ ተናግሯል፡፡
 
በወጣት የተገነባ ቡድን ለስኬት ቁልፍ መሆኑን የዚህ አመቱን ባርሴሎና እና ፒ ኤስ ጂን በማሳያነት የሚያነሳው አሰልጣኙ ሼሽኮ የአርሰናል ቀዳሚው ምርጫ ሊሆን እንደሚገባ ገልጿል፡፡
 
በተጨማሪም ቤንጃሚን ቬሽኮ አርሰናል ለሚፈልገው የረጅም ጊዜ የቡድን ግንባታ ወሳኝ ስለመሆኑ አስረድቷል።
 
ዘ አትሌቲክ ያናገረው ወኪል ደግሞ የተለየ ሀሳብ አለው ለአርሰናል በዚህ ሰአት ከቪክቶር ጊዮኬሬሽ የተሻለ አጥቂ የለም ይላል፡፡ በዚህ ሳምንት 27 አመት የሚሆነው ስዊዲናዊ አጥቂ ግብ በማስቆጠር ከሼሽኮ ጋር ፍጹም የሚነጻጸር አይደለም።
 
ብራይተንን ጨምሮ በተለያዩ የእንግሊዝ ክለቦች በውሰት ያሳለፈው ተጫዋች በሁለት አመት የስፖርቲንግ ሊዝበን ቆይታው በ102 ጨዋታ 97 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡
 
በዚህ አመት አውሮፓ ላይ ከፍተኛ ግብ በማስቆጠር ቁጥር አንድ ላይ የተቀመጠ አጥቂ ለዚያውም ከሼሽኮ ባነሰ የዝውውር ዋጋ አግኝቶ አለማስፈረም እና አሁንም ስለ ቡድን ግንባታ ማሰብ በቀጣይ አመት ዋንጫ ለሚፈልግ ቡድን ምክንያታዊ ሊሆን እንደማይችል አስረድቷል፡፡
 
አርሰናልን ወደ ሚፈልገው አቅጣጫ ለመውሰድ የክለቡ ስፖርቲንግ ዳይሬክተር እና አሰልጣኙ በአንድ አቅጣጫ መቆም አለባቸው የሚሉት ደግሞ የቀድሞው የእንግሊዝ እግር ኳስ ማህበር የቴክኒክ ዳይሬክተር ለስሊ ሪድ ናቸው።
 
ምንም እንኳን በሌላ ሊግ ስኬታማ የሆነ ተጫዋች ወደ እንግሊዝ ሲያመራ ምን ሊገጥመው እንደሚችል መገመት ከባድ ቢሆንም ለአርሰናል የአጭር ጊዜ ስኬት ትክክለኛው አጥቂ ጊዮኬሬስ መሆን እንዳለበት አንጋፋው የእግር ኳስ ባለሙያ ከዘ አትሌቲክ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
 
አመቱን ያለ ዋንጫ ያጠናቀቀው አሰልጣኝ ሚካኤል አርቴታ በርካታ ግቦችን ካስቆጠረው ጊዮኬሬሽ ይልቅ ቤንጃሚን ሼሽኮን እንደሚፈልግ በግልጽ መናገሩ ከአንድሪያ ቤርታ ጋር ግልጽ ልዩነት እንዳላቸው የተቀመጠ ማሳያ ነው።
 
በገጠመው የአጥቂ ችግር ምክንያት በአስገዳጅ ሁኔታ ካይ ሀቨርዝን የመጨረሻ አጥቂ አድርጎ የተጠቀመው ስፔናዊው አሰልጣኝ የሼሽኮ ወደ አርሰናል መምጣት የሀቨርዝን ግልጋሎት በሚገባ ለማግኘት እንደሚያግዝ ይገልጻል።
 
ሀቨርዝ ከመጨረሻ አጥቂ ይልቅ ከጀርባ ሆኖ ሲሰለፍ በብዙ ስኬታማ እንደሚሆን ያሳወቀው አርቴታ በተለይ ከሼሽኮ ጋር የሚኖራቸው ጥምረት ይበልጥ አስፈሪ የፊት መስመር ለመገንባት ቁልፉ ጉዳይ እንደሚሆን ያምናል።
 
በአትሌቲኮ ማድሪድ ቤት እንደ አንቱዋን ግሪዝማን፣ ዲየጎ ኮስታ፣ ሁሊያን አልቫሬዝ እና ሌሎች ተጽዕኖ ፈጣሪ አጥቂዎች እንዲፈርሙ ያደረገው አዲሱ የአርሰናል ስፖርቲንግ ዳይሬክተር አንድሪያ ቤርታ ጊዮኬሬስ እንዲፈርም ይፈልጋል።
 
አሁን ጥያቄው መድፈኞቹ በፕሪሚየር ሊግ ያልተፈተነውን ግብ አስቆጣሪ ቪክቶር ጊዮኬሬስን ያስፈርማሉ ወይንስ ደግሞ የረጅም ጊዜ እቅድ ሊሆናቸው የሚችለውን ቤንጃሚን ሼሽኮን ወደ ሰሜን ለንደን ይወስዳሉ የሚለው ነው።
 
ተገማች ባልሆነው የተጫዋቾች ዝውውር በአርሰናል ራዳር ውስጥ የሚገኙት ሁለቱ አጥቂዎች በሌሎች ክለቦች አለመጠለፋቸውንም ማረጋገጥ ባይቻልም የአንድሪያ ቤርታ እና ሚካኤል አርቴታ እንዲሁም የደጋፊዎች የክርክር ማዕከል ሆኖ የቀጠለው ጉዳይ ምን አልባትም በመጭዎቹ ቀናቶች መልስ ሊያገኝ ይችላል።
 
በአንተነሀ ሲሳይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top