ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከደቡብ አፍሪካው አቻቸው ጋር በነበራቸው ውይይት መሐል ቴሌቪዥን ያስከፈቱበት ክስተት

1 Day Ago 1790
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከደቡብ አፍሪካው አቻቸው ጋር በነበራቸው ውይይት መሐል ቴሌቪዥን ያስከፈቱበት ክስተት

አሜሪካ በዋሽንግተን የነበሩትን የደቡብ አፍሪካን አምባሳደር በቅርቡ አባርራለች።

በተጨማሪም ለደቡብ አፍሪካ የምታደርገውን የውጭ ዕርዳታ በማቋረጥ ተጨማሪ የ30 በመቶ ታሪፍ እንደምትጥልባት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጠቁመው ነበር።

ይህም ብቻ አይደለም አሜሪካ በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ ነጭ ዜጎች ላይ ይፈጸማል ባለችው በደል እና 'የዘር ማጥፋት' የተነሣ የሀገሪቱን መንግሥት ክፉኛ ስትወነጅል ሰንብታለች።

በእርግጥም በአፍሪካ ጉዳዮች በአንፃራዊነት ሰፊ ትኩረት የለውም የሚባለው የትራምፕ አስተዳደር በደቡብ አፍሪካ ላይ ባልተለመደ መልኩ ትኩረት ሲያደርግ መቆየቱን ብዙዎች ይናገራሉ።

ሁለቱ ሀገራት በእስራኤል እና ፍልስጤም ጉዳይ ላይ ሰፊ ልዩነት ያላቸው ሲሆን፣ የደቡብ አፍሪካ የብሪክስ መሥራች አባልነት እና ከሩሲያ ጋር ያላት እንቅስቃሴም አሜሪካን እንደሚያሳስባት ‘ካውንስል ኦፍ ፎሬይን ሪሌሽንስ’ የተሰኘው እና በፖለቲካ እና የውጭ ጉዳይ ግንኙነቶች ላይ አተኩሮ የሚሠራው አማካሪ ቡድን ባወጣው ጸሑፍ አስነብቧል።  

ይህን ሁሉ ውጥረት ያረግባል ተብሎ የተጠበቀውን ውይይት ለማድረግ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ወደአሜሪካ አቅንተው ነበር። ራማፎሳ ዋሽንግተን የደረሱት የትራምፕን ለማግባባት አስበው እንደሆነ በስፋት ሲዘገብ ቆይቷል።

ለዚህም ከትራምፕ ጋር ቀረቤታ አላቸው ተብለው የሚታሰቡትን  ነጭ የጎልፍ ተጫዋቾቹን ኤርኒ ኤልስ እና ሬቲፍ ጉሰን እንዲሁም ነጩን ደቡብ አፍሪካዊ ቢሊየነር እና የቅንጦት ዕቃዎች ነጋዴውን ዮሃን ሩፐርትን ይዘው ነው በኋይት ሐውስ የተገኙት።

ይሁንና የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ውይይት እንደተጠበቀው ሳይሆን አለመግባት የተስተዋለበት እንደነበር ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ይገኛሉ።

የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በነጩ ቤተመንግሥት የትራምፕ ቢሮ በሰላምታ ቢጀምሩም በመሐል ግን ባልተጠበቀ ሁኔታ ዶናልድ ትራምፕ ዝግጅት ባደረጉበት አግባብ ረዳታቸውን መብራቶቹን እንዲቀንሱ እና ቴሌቪዥኑን እንዲከፍቱ አዘዙ።

ቴሌቪዥኑ ሲከፈትም በደቡብ አፍሪካ ነጮች ላይ ይፈጸማል ስለተባለው ጥቃት እና የተለያዩ ችግሮች የሚያወሱ ዜናዎች እና ጥያቄዎችን የያዙ ቪዲዮዎች ይታዩ ጀመር።

ያኔ በደቡብ አፍሪካ የተወለደው አሜሪካዊው ቢሊየነር ኢሎን መስክ፣ ከሶፋ ጀርባ ሆኖ በፀጥታ ይመለከት ነበር።

የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የሠሯቸውን ዘገባዎች በወረቀት የያዙት ትራምፕ አንድ በአንድ ለደቡብ አፍሪካው መሪ በማሳየት ቅሬታቸውን ገለጹ።  

ትራምፕ በነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ላይ ይደርሳል ስለተባለው ስደት እና ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ የተቀነባበረ የክስ ናዳ ማዝነባቸውን ቀጠሉ።

ልክ የዩክሬኑ መሪ ቮሎድሚር ዘለንስኪ በየካቲት ወር በኋይት ሐውስ በነበራቸው ጉብኝት ወቅት የነበረውን ያልተገባ የውይይት መድረክ የሚያስታውስም ሁነት ተፈጥሮ ነበር። 

ትራምፕ በተደጋጋሚ በአሜሪካ ነጭ ገበሬዎች ላይ የሚደርሱ በደሎችን እያነሡ ቢከራከሩም ራማፎሳ ግን በሰከነ ስሜት ውስጥ ሆነው ነበር።

ራማፎሳ በውይይቱ መሐል ልዑካቸውን የተቀላቀሉትን ነጭ የደቡብ አፍሪካ ጎልፍ ተጫዋቾች እና ነጩን ቢሊየነርን በመጠቆም "የነጭ ገበሬዎች የዘር ማጥፋት ቢኖር ኖሮ፣ በእርግጠኝነት ልነግርዎት እችላለሁ፤ እነዚህ ሦስቱ ክቡራን እዚህ አይገኙም ነበር" በማለት ለትራምፕ ክስ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

በተጨማሪም ነጩ የደቡብ አፍሪካ የግብርና ሚኒስቴር እንዲሁም ቢሊየነሩ የራማፎሳ ልዑክ አባል በነጭ ገበሬዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ሆን ተብሎ የሚፈጸም ሳይሆን በሌሎች ዓለማትም ያለ ወንጀል መሆኑን የራማፎሳ መንግሥት ተጠያቂ ሊሆን እንደማይገባ ማስተባበያ ለመስጠት ጥረት አድርገው ነበር።

ዶናልድ ትራምፕ በነጭ ገበሬዎች ላይ ይደርሳል ስለተባለው ጥቃት ሲያመለክቱ፣ "ሞት፤ አሁንም ሞት፤ አሰቃቂ ሞት ይደርስባቸዋል" ብለዋል። ሲሪል ራማፎሳ በበኩላቸው፣ “በሀገሪቱ ያለው ወንጀል ከየትኛውም የኅብረተሰብ ክፍል የመጡ ዜጎችን ዒላማ ያደረገ ነው” ሲሉ መልሰውላቸዋል።

በውጥረት የተሞላው ውይይት ግን መጨረሻ በቀልድ እና በፈገግታ ታጅቦ በሰላማዊ ሁኔታ ነበር የተጠናቀቀው።

በጌትነት ተስፋማርያም

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top