ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በዛሬው ዕለት መርቀው ከፍተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልእክት፤ በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ዜጎቻችን ላይ ምሬት የሚፈጥሩ አሰራሮችን ፈትሾ ማስተካከል ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል።
ለዚህም ማሳያ የሆነውን የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዛሬ መመረቁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
ይኽን አዲስ ማዕከል የሚገልጡ ሶስት ቁልፍ አላባውያን አሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የቆየ እና የተጎዳ ህንፃን ወደ ዘመናዊ እና ሥነውበታዊ ደረጃው ለሥራ ከባቢ አስደሳች ወደ ሆነ ህንፃ መለወጡ አንዱ ነው ብለዋል።
አገልግሎቶችን ለመሰተር እና ለማቀናጀት በሀገር ውስጥ የለማ ሶፍትዌር በሥራ ላይ መዋሉ ብሎም በታደሰ አመለካከት ብቁ እና ክብር የሞላበት አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶች መዘጋጀታቸው ሌሎቹ አላባውያን ናቸው ሲሉም ጠቁመዋል።
12 ተቋማት በአንድ ጣሪያ ሥር 40 የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት መጀመራቸውን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይኽም ዜጎች ጊዜያቸውን እንዲቆጥቡ እና አገልግሎቶችን በተሻለ ውጤታማ መንገድ ለማግኘት ያግዛል ነው ያሉት።
እንደዚህ ያሉ ሥርዓቶችን ማበልፀግ ለዜጎች የተለያዩ የአገልግሎት ርካታ መታጣቶች ምላሽ በመስጠት በሂደት ለሰፊው ማኅበረሰብ ርካታ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸውም አስገንዘበዋል።
የዛሬው ምረቃ ትልቅ ርምጃ መራመዳችንን ያሳያል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ኢትዮጵያ በዚህ ማዕከል ላይ ጨምራ እና አስፋፍታ ለዜጎች ሁሉ የተሻለ የአገልግሎት አሰጣጥን ታረጋግጣለች ሲሉም ገልጸዋል።