በምሽት የንግድ እና የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያደርገው ደንብ ለማኅበረሰቡ አዲስ የሥራ ባህል የሚያላብስ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ሀቢባ ሲራጅ ገለጹ።
“የከተማ ልማት እና የንግዱ እንቅስቃሴ የአንድ ሣንቲም ሁለት ገፅታ ናቸው” ያሉት ኃላፊዋ፣ መዲናዋ በለውጥ የተላበሰችው ገፅታ አዲስ አሠራር፣ ዘመናዊ እና ያደገ የንግድ ማኅበረሰብን የሚፈልግ ነው ሲሉ ለኢቢሲ ዶትስትሪም ገልጸዋል።
የንግድ ሰዓት ማሻሻል እና ገቢ መጨመር መቻል ለልማት ከፍ ያለ አበርክቶ እንዳለው በመግለጽ፤ ለ8 ሰዓታት ብቻ በመሥራት በንግዱ ማኅበረሰብ ዘንድ አመርቂ ዕድገት ማስመዝገብ እንደማይቻል ነው የገለጹት።
በዚህ ዙሪያ ‘የመኖሪያ ቤታቸው እና የንግድ ሱቃቸው የሚራራቅ ነዋሪዎች ጉዳይ ከግንዛቤ ገብቷል ወይ?’ ስንል ጠይቀናቸዋል።
ኃላፊዋም ደንቡ በበቂ ጥናት እና ጥምረት እንደሚተገበር በማንሣት በተለይ የፀጥታ እና ትራንስፖርት ጉዳይ በዋናነት ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ገልጸዋል።
ከትራንስፖርት አገልግሎት ጋር በተያያዘ ስምሪት እንደሚደረግ እንዲሁም ምሽቱን ተከትሎ ማንኛውም የታሪፍ ጭማሪ እንደማይኖር ተናግረዋል።
ለዚህም በቦታው የሚኖሩ የስምሪት ሠራተኞች መኖራቸውን ነው የገለጹት።
በዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ በሮ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በቅንጅት እየሠሩ ነው ብለዋል።
ከደኅንነት ጋር በተያያዘ መዲናዋ የመከላከያ ሠራዊት መቀመጫ ከመሆኗ ባሻገር ማኅበረሰቡ በጋራ በመሆን በየብሎክ ጥበቃ የሚያደርግ በመሆኑ የደኅንነት ስጋት እንደማይኖር ነው የተናገሩት።
የንግድ ቢሮ ‘አቅርቦት ካለ ፍላጎት ይፈጠራል’ ብሎ ያምናል የሚሉት ኃላፊዋ፤ “እስከ ምሽት ባለው ቆይታ ተገልጋይ አናገኝም” የሚለው ቅሬታ በጊዜ ሂደት የሚቀረፍ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ደንቡ ከመተግበሩ በፊት ከ77 ሺህ በላይ የሚሆኑ የንግዱ ማኅበረሰብ የተወያዩበት እና አሠራሩን የሚፈልጉት መሆኑን በውይይቱ ወቅት መግለጻቸውን አስረድተዋል።
ማኅበረሰብን ከነበረበት ልምድ አላቅቆ አዲስ አሠራር ለማስለመድ ጊዜ እንደሚፈልግ የጠቀሱት ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ፣ የደንቡ ተግባራዊነት ሲጠናከር እና የታሰበው ውጤት ሲመዘገብ ጠንካራ የሥራ ባህል የተላበሰ ማኅበረሰብ ይኖረናል ሲሉ ገልጸዋል።
በአፎሚያ ክበበው