የናሳ የጠፈር ተመራማሪ የሆኑት ቡች ዊልሞር እና ሱኒ ዊሊያምስ ከ286 ቀናት የጠፈር ላይ ቆይታ በኋላ ወደ ምድር መመለሳቸው ተገልጿል።
ሁለቱ ተመራማሪዎች እ.ኤ.አ ሰኔ 2024 ወደ ጠፈር ማቅናታቸው የሚታወስ ነው።
ታሪካዊ የጠፈር ጉዞ በማለት የተሰየመው ተልዕኳቸው መቋጫውን በሜክሲኮ ባሕረ ሰላጤ ላይ አድርጓል።
ተመራማሪዎቹ የቦይንግ ስታር ላይነር የጠፈር መንኮራኩር ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት ለሚደረግ ሙከራ ለአንድ ሳምንት ወደ ጠፈር ማቅናታቸው የሚታወስ ነው።
ሆኖም ግን በተፈጠረ የቴክኒክ ችግር ምክንያት ከታቀደው ቀን በላይ ሊቆዩ ችለዋል።
በዚህም ምድርን ከ4 ሺህ 500 ጊዜ በላይ የዞሩ ሲሆን፤ ይህ በድምሩ 195 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ይደርሳል።
ሱኒ ዊሊያምስ 62 ሰዓታትን ከጠፈር መንኮራኩር ውጪ በሚከወን ተልዕኮ ላይ ያሳለፈች ሴት በመሆን ክብረወሰን አስመዝግባለች።
በቆይታቸው ከምድር ይዘው የሄዱት መሰረታዊ ፍላጎቶች በተለይም ምግብ ለ3 ወራት ብቻ እንዳቆያቸው የተገለጸ ሲሆን፣ የተቀሩትን ጊዜያት በዓለም አቀፉ የሕዋ ጣቢያ (አይ.ኤስ.ኤስ) መጠባበቂያ ተብሎ ከተቀመጠ ምግብ ላይ መጠቀማቸው ተጠቁሟል፡፡
በጣቢያው በቀን ለአንድ ሰው የሚሆን 3 ነጥብ 8 ፓውንድ መጠባበቂያ ምግብ መኖሩ ተመላክቷል፡፡
ተመራማሪዎቹ ከአስፈላጊ የጤና ምርመራ እና የእረፍት ጊዜ በኋላ ለቀጣይ ተልዕኮዎች ስኬት ያገኟቸውን ጠቃሚ ልምዶች እና የገጠሟቸውን እክሎች እንደሚያጋሩ ይጠበቃል።