ኢትዮጵያ በታሪኳ የማንንም ድንበር ገፍታ የትኛውንም ሀገረ ወርራ አታውቅም።
ይህ ታሪኳ ግን ከተደጋጋሚ የመወረር ሙከራዎች አላዳናትም። ኢትዮጵያውያን የትኛውም ግዙፍ ወራሪ ቢመጣ ሀገራቸውን አሳልፈው እንደማይሰጡ ያስመሰከሩበት ድል ደግሞ የዓድዋ ድል ነው።
ያ ድል የአንዱ ጣሊያን ሽንፈት ብቻ ሳይሆን የመላው ቅኝ ገዢዎች ሽንፈት ነበር።
ኢትዮጵያ የፈነጠቀችው ያ የድል ነፀብራቅ በቅኝ ግዛት መከራ ውስጥ ለነበሩት አፍሪካውያንም የነፃነት ትግላቸው የማንቂያ ደወል ሆነ።
ያኔ መራራ ሽንፈት የደረሰባት ጣሊያን ታዲያ ያን ሽንፈት 40 ዓመት ሙሉ ስታስብ ቆየች።
40 ዓመታትን ስትዘጋጅ ከርማም በ1928 ዓ.ም ዳግመኛ ኢትዮጵያን ወረረች። ቀድሞውንም የሰውን የማይፈልገው፣ ሲመጡበት ግን እንዴት እንደሚመክት የሚያውቀው የኢትዮጵያ ሕዝብም የጣሊያንን ወረራ ለመመከት በአንድነት ተነሣ።
በዚህ ወቅት በሰሜን እና በምሥራቅ በተካሄዱ ጦርነቶች ግን ለጊዜው ድል አልቀናቸውም።
ለኢትዮጵያ ጦር መፈታት ከአመራር ጀምሮ የተለያዩ ውስጣዊ እና ውጫዊ ተግዳሮቶች ምክንያት ቢሆኑም ጣሊያን ካለፈው ሽንፈቷ ተምራ ያደረገችው ዝግጅት ትልቁን ድርሻ የሚይዝ መሆኑን የታሪክ ተመራማሪዎች ይናገራሉ።
ንጉሡ የተሳተፉበት የማይጨው ጦርነትም የመጨረሻው የተደራጀ ፍልሚያ ሆኖ ጣሊያን ድል ያገኘችበት ሆኖ ተጠናቀቀ።
የነፃነትን ትርጉም በአግባቡ የሚያውቁት ኢትዮጵያዊያን ግን በመድፍ እና በአውሮፕላን መርዝ በታገዘው የጣሊያን ጦር ተሸነፍን ብለው ተስፋ ቆርጠው አልተቀመጡም።
ኢትዮጵያውያን ዐርበኞች ምንም እንኳን ከማዕከል የሚመራቸው አካል ባይኖርም በየአካባቢያቸው ተደራጅተው ጣሊያንን መፋለም ጀመሩ።
እነ ራስ አበበ አረጋይ፣ ኮሎኔል አብዲሳ አጋ፣ ሌ/ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ፣ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ፣ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ፣ ዐርበኛ ሸዋረገድ ገድሌ፣ ፊታውራሪ ጌጃ ገርቦ፣ ደጃዝማች ዑመር ሰመተር እና ሌሎችም በየአካባቢያቸው ለጣሊያን የእግር እሳት ሆኑ።
እንደነ አቡነ ጴጥሮስ ያሉ የሃይማኖት አባቶች “እንኳን ሕዝቡ የኢትዮጵያ ምድር ለባዕድ እንዳይገዛ” አውግዘው መሥዋዕትነት ከፍለው ለኢትዮጵያ ወደቁ። በርካታ ቆራጦችም የዐርበኝነት ትግል ለማካሄድ ወደ ዱር ተመሙ።
ለባዕድ እንዳይገዛ የተገዘተውን የሀገራቸውን መልክዓ-ምድር መመኪያ አድርገው ጣሊያንን ይፋለሙ ጀመሩ።
የአዲስ ዘመንን መረጃ ዋቢ ስናደርግ በበጌምድር እና አካባቢው ራስ ውብነህ ተሰማ እና ቢትውደድ አዳነ፤
በጎጃም ቢትወደድ መንገሻ ጀምበሬ፣ በላይ ዘለቀ (አባ ኮስትር)፣ ደጃዝማች ኃይለየሱስ ፍላቴ እና ራስ ኃይሉ በለው፤
በሸዋ ራስ አበበ አረጋይ፣ መስፍን ስለሺ ፀሐይ ዕንቁሥላሴ፤ የበሼ ቤተሰቦች ደጃች ተሾመ እና አበበ ሽንቁጥ፤
በወሎ እነ ኃይሉ ከበደ፣ ወሰን ኃይሉ እና በሌሎች በኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ ዐርበኞች ሕዝቡን በማስተባበር ጣሊያንን የረገጣት የኢትዮጵያ ምድር ረመጥ እንድትሆንበት አደረጉ።
ከአምስት ዓመት መራር ተጋድሎ በኋላም ጣሊያን ድጋሚ ተሸንፋ ከኢትዮጵያ ምድር ተባረረች።
በግፍ ኢትዮጵያን የወረረችው ጣሊያን በወቅቱ በነበረው የሁለተኛው ዓለም ጦርነት አሰላለፍ ከሂትለር ጎን መሰለፏ ደግሞ ውድቀቷን አፋጠነው።
ይህም የማንንም ሐቅ የማትገፋው ኢትዮጵያን የነካ ፈጣሪም ዝም እንደማይለው ማሳያ ነው ይላሉ ኢትዮጵያውያን።
እንግሊዝ የነበሩት ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴም በወቅቱ በነበረው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከጣሊያን ተቃራኒ በተሰለፈችው እንግሊዝ ወታደሮች ታጅበው ሱዳን ገቡ። በሱዳንም ኢትዮጵያውያን ዐርበኞች ተቀላቀሏቸው።
ጣሊያንን ተክተው ኢትዮጵያን በእጃቸው ማቆየት የፈለጉት የእንግሊዝ የጦር መሪዎች በወቅቱ ንጉሡ እንደፈለጉ ወደ ሀገር እንዳይገቡ ብዙ መሰናክል ይፈጥሩ እንደነበር ይነገራል።
ጉዳዩ ከርሮ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ቸርችል እና የእንግሊዝ ፓርላማ ደርሶ እንደነበርም የታሪክ መዛግብት ያወሳሉ።
ንጉሡን አጅበው ከመጡት የእንግሊዝ ጦር መሪዎች መካከል ግን ጄኔራል ዊንጌት ይህን አሻጥር ከሚቃወሙት እና ካጋለጡት መካከል ነበሩ።
በንጉሡ የሚመራው እና የዐርበኞች እና የእንግሊዝ አማካሪዎች የሚገኙበት ‘ጌዲዮን’ ተብሎ የተሰየመው ጦር ከሱዳን ተነስቶ በኦሜድላ አልፎ በጎጃም በኩል ወደ መሐል አገር ገሠገሠ።
ፈተናው ሁሉ ታልፎም ንጉሡ እና ዐርበኞች ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም አዲስ አበባ ገቡ። ይህ ቀን የተከበረ እና የተቀደሰ፣ በየዓመቱም ታላቁ የኢትዮጵያ በዓል ሆኖ የሚውልበት ነው።
በዚህም ቀን ለሚወድዷት ሀገራቸው ነፃነት እና ለሰንደቅ ዓላማቸው ክብር አባቶቻቸው የተላለፈውን ጥብቅ አደራ አናስወስድም በማለት መሥዋዕት ሆነው ደማቸውን ያፈሰሱትን አጥንታቸውን የከሰከሱትን ጀግኖቻችንን እናስታውሳለን።
ይህ ዐርበኞች መታሰቢያ ዘንድሮ ለ84ኛ ጊዜ ተከብሯል። የዘመኑ ትውልድ የዐርበኞችን መታሰቢያ ሲያከብር ዘመኑ የሚጠይቀውን የዐርበኝነት ተጋድሎ በመፈጸም መሆን እንዳለበት ጀግኖች ዐርበኞች ይመክራሉ።
በለሚ ታደሰ