የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት(ተመድ) የዘላቂ ልማት መፍትሔ ጥምረት የአፍሪካ ቢሮውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር ከፈተ።
ጥምረቱ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) እና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ዛሬ ይፋ አድርጓል።
የተመድ የዘላቂ ልማት መፍትሔ ጥምረት ለዘላቂነት ልማት እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን ለመፍታት በዓለም ዙሪያ ያሉ የፈጠራ ልሂቃንና የቴክኒክ ባለሙያዎች ያሰባስባል።
በአዲስ አበባ የተከፈተው የጥምረቱ ቢሮም የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማከናወን ለፖሊሲ አውጭዎች ግብዓት የሚሆኑ ሳይንሳዊ መፍትሔዎችን ያቀርባል ተብሏል።
የጥምረቱ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጀፍሪ ሳክስ እንዳሉት፣ የጥምረቱ ተቀዳሚ ዓላማ በዓለም ላይ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና እና ማህበራዊ ፍትህ ማስፈን ነው።
መንግስታትን መደገፍ ዘላቂ የልማት ግቦችን ማሳካት በመሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መፍትሔ በማፈላለግ ላይ ሊያተኩሩ ይገባል ብለዋል።
በአዲስ አበባ በይፋ የተከፈተው የዘላቂ ልማት መፍትሔ ጥምረት ቢሮም አፍሪካ ተደራሽ ለማድረግ ያለመ መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት መስራት የዓለም ስልጣኔ ፈርቀዳጅ መሆኗን የገለጹት ጀፍሪ ሳክስ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች መሆኑንም ተረድቻለሁ ብለዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) የዘላቂ የልማት ግቦች የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 ን ከግብ ለማድረስ ቁልፍ መንገድ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በጥናትና ምርምር የላቀ አገልግሎት እንዳለው የገለጹት ተጠባባቂ ፕሬዝዳንቱ የዘላቂ ልማት መፍትሔ ጥምረቱ ተጨማሪ አቅም ስለሚሆነው በትብብር እንሰራለን ለዚህ ደግሞ ቁርጠኛ ነን ብለዋል።