ትንሣኤ የራቀው የኢትዮጵያ እግር ኳስ

3 Days Ago 7920
ትንሣኤ የራቀው የኢትዮጵያ እግር ኳስ

ዓለም ላይ ከደቡብ ኮሪያ ብሔራዊ ቡድን በመቀጠል ለረጅም ዓመታት ዋንጫ ማየት ያልቻለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነው፡፡ 

የኤዥያዋ ሀገር  የአህጉሩን  ትልቅ ዋንጫ ካነሳች 65 ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ ምንም እንኳን ደቡብ ኮሪያ ዋንጫ ካነሳች ረጅም  ዘመን ብታስቆጥርም በኤዥያ ዋንጫ 4 ጊዜ የፍጻሜ ተፋላሚ እንዲሁም 3 ጊዜ ደግሞ 3ኛ ደረጃን ይዛ በማጠናቀቅ ጠንካራ ተፎካካሪ ብሔራዊ ቡድን እንዳላት አሳይታለች፡፡

በተጨማሪም በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ተጽዕኖ መፍጠር የቻሉ እንደ ሶን ሁንግ፣ ሚን ሊ፣ ካንግ ኢን፣ ኮሚ ሚን፣ ጄይ ሁዋንግ፣ ሂ ቻን እና ሌሎችንም ለዓለም አስተዋውቃለች፡፡ 

የአፍሪካ እግር  ኳስ መስራች  ሀገር  ኢትዮጵያ ደግሞ የአህጉሩን ዋንጫ ከነሳች 63 ዓመታት ሆኗታል፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት አይደለም ቅንጦት ስለሚመስለው  እግር ኳስ ማሰብ  ይቅርና ከቅኝ ግዛት ሙሉ ለሙሉ ባልተላቀቁበት 1950ዎቹ  የአህጉሩን እግር ኳስ በመመስረት ትልቁን ሚና ብትጫወትም ጉዞዋ ግን የጅማሮዋን ያህል አልሆነም፡፡ 

ከአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ምስረታ 5 ዓመት በኋላ በ1954 ዓ.ም በኢትዮጵያ አዘጋጅነት የተካሄደው እና  4 ሀገራት የተካፈሉበት መድረክ  ኢትዮጵያ  የአፍሪካ ዋንጫን ለመጀመርያም ለመጨረሻም ጊዜ ያሳካችበት ነው፡፡ 

ከዚህ ጊዜ በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከተሳትፎ ያልፈ ነገር ማሳየት አልቻለም፡፡ ዋልያዎቹ ከ1954ቱ መድረክ በኋላ እስከ 1974ቱ የሊቢያ አፍሪካ ዋንጫ ወጣ ገባ እያሉ ቢሳተፉም ከዚህ ጊዜ በኋላ ያሉት ዓመታት ግን ኢትዮጵያ በመሰረተችው እግር ኳስ "የበይ ተመልካች" ለመሆን የተገደደችባቸው ናቸው፡፡ 

አይደለም በትልልቅ  መድረኮች መሳተፍ ይቅርና ማጣሪያዎችን ማለፍ  እንኳን  "ተራራ የመግፋት" ያህል ከባድ ሆኖባታል፡፡

አሁን ጥቄው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምን ገጠመው? የሚለው ነው፡፡ እስቲ እዚህ ላይ ትንሽ እንቆይ። 

ለብሔራዊ ቡድኑ ውጤት ማሽቆልቆል በርካታ ምክንያቶችን መጠቀስ ይቻላል፡፡  የመጀመርያው  የሀገሪቱ እግር ኳስ ከታዳጊዎች ጀምሮ እስከ ክለቦች  የሚመራበት  መንገድ በኋላ ቀር መሆኑ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያለች የአህጉር እግር ኳስ መስራች እና ከ120 ሚሊየን በላይ ህዝብ ያላት ሀገር አንድም እንኳን ደረጃውን የጠበቀ ታዳጊዎች የሚሰለጥኑበት የእግር ኳስ አካዳሚ የላትም፡፡

በእግር ኳሱ ዙሪያ ያሉ ባለሙያዎች  እንዲህ አይነት መሰረታዊ  ጉዳዮችን ከማስፈጸም ይልቅ  የግል ጥቅምን ማሳደድ ላይ የተጠመዱ መሆናቸው ችግሩን ከድጡ ወደ ማጡ አድርጎታል፡፡ 

ለማሳያ ያክል ከ5 ዓመት በፊት በተሰራ ጥናት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ በዓመት ከ2.2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ ይደረጋል፡፡ ይህ እንግዲህ ከ5 ዓመት በፊት ማለት እንደ አሁን የተጫዋቾች የደመወዝ መጠን በብዙ ዕጥፍ ከማደጉ በፊት፡፡ በዓመት  ለእግር ኳሱ ብቻ ይሄንን ያክል 'ረብጣ' ገንዘብ የምታወጣ  ሀገር  ጉዞዋ ግን  ወደ  ኋላ ነው፡፡

የሚገርመው  ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑት ክለቦች  የመንግሥት መሆናቸው ነው፡፡  ይሄ ማለት እግር ኳስ ሀብት ሆኖ  ወደ ንግድነት በተቀየረበት ዓለም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ግን  ዓመት ጠብቆ  የሚሰጠውን በጀት ብቻ እያጠፋ የሚጓዝ መሆኑ  ጠያቂም ተጠያቂም እንዳይኖር አድርጎታል፡፡ 

በወር ለአንድ ተጫዋች  ከ600 እስከ 700 ሺህ ብር የሚከፍሉ ክለቦች ባሉበት ሀገር  ብሔራዊ ቡድኑ ግን መለያው ሽንፈት ብቻ ነው፡፡  በቅርቡ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር  የክለቦች የገንዘብ አስተዳደር መመሪያን  በተመለከተ በጀመረው ማጣራት የተፈጸሙ የገንዘብ ምዝበራዎች እንዲሁም  የተጫዋቾች ዝውውር  እና  የአሰልጣኞች ቅጥር ላይ የሚፈጸሙ ከህግ ውጭ የሆኑ ጉዳዮችን  ለማስቆም  የገንዘቡ ባለቤት መንግሥትም ነገሩን ቆም ብሎ የሚያጤንበት ትክክለኛ ጊዜ ላይ እንዳለ ማሳያ ነው፡፡ በየዓመቱ የሚመደበው ገንዘብ  ምን ላይ? ለየትኛው ጉዳይ? እንደዋለ እስካልተመረመረ ድረስ ዘርፉ ከወደቀበት መነሳቱ ቀርቶ  የተወሰኑ ተዋናዮች የሀብት ማካበቻ  ሆኖ መቀጠሉ የማይቀር ነው፡፡

ሌላኛው ጉዳይ ከተመሰረቱ 70 እና 80  ዓመታትን  የተሻገሩ  የእግር  ኳስ  ክለቦች   የራሴ የሚሉት ሜዳ የላቸውም፡፡ የክለቦቹ አደረጃጀት በራሱ ዓለም ከሚጓዝበት ፍጹም ተቃራኒ ነው፡፡ የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር ፊፋም ይሁን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (ካፍ) ያስቀመጡትን የክለቦች መመዘኛ ማሟላት የሚችል  አንድም ክለብ የለም፡፡

እዚህ ላይ  ትልቁ ሃላፊነት ደግሞ የሀገሪቱ እግር ኳስ የበላይ አስተዳዳሪ አካል  የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ነው፡፡ ክለቦች ለዓመታት እንደፈለጉ ሲሆኑ  አደረጃጀታቸውን እና የሚጓዙበትን መንገድ መፈተሽ ባለመቻሉ አሁን ላይ ለተፈጠረው  የብሔራዊ  ቡድኑ  ውድቀት ቀዳሚ ተጠያቂ ያደርገዋል፡፡

ምን አልባት በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ኢትዮጵያ አንድም ደረጃውን የጠበቀ ስቴዲየም እንዳይኖራት ለመሆኑ መንግሥትን ጨምሮ ተጠያቂ ቢሆንም በኋላ ቀር መንገድ የሚጓዙት ክለቦችም ድርሻቸው ትልቅ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡

የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች ቅጥርም ሌላኛው ለውጤቱ  መጥፋት  ምክንያት  የሆነ  ጉዳይ ነው፡፡

ባለፉት 25 ዓመታት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ጊዜያዊዎቹን እና በድጋሜ የሾማቸውን ጨምሮ 24 አሰልጣኞችን ቀያይሯል፡፡ ችግሩ አሰልጣኝ መቀያየሩ ሳይሆን ከጅምሩ አሰልጣኞቹ የሚሾሙበት መንገድ ግልጽ አይደለም፡፡

የትኛው የውጤት ታሪካቸው ወይንም  የጨዋታ መንገዳቸው ተገምግሞ ሃላፊነት እንደሚሰጣቸው ተጨባጭ ምክንያት ማቅረብ አይቻልም፡፡

በዘመናዊ እግር ኳስ አንድ አሰልጣኝ በትንሹ ስኬታማ ለመሆን አራት ዓመት እና ከዚያ በላይ ያስፈልገዋል፡፡ በኢትዮጵያ ነበራዊ ሁኔታ ግን ይሄ አይሰራም ለቅጥሩም ለስንብቱም በቂ ምክንያት የለም፡፡

ከዚሁ ጋር በተገናኝ የሚነሳው አንድ ጉዳይ ትኩረት አለመስጠት ነው፡፡ ከወቅቱ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በፊት  የነበሩት ገብረ መድህን ሃይሌ ወደ ብሔራዊ ቡድን ሃላፊነት  ሲመጡ የቀድሞ ስራቸውን አለመልቀቃቸው ግርምትን የፈጠረ ሆኖ አልፏል፡፡ 

'ሁለት እግር አለኝ ተብሎ' ሁለት ዛፍ ላይ ይወጣ ይመስል አሰልጣኙ ኢትዮጵያ መድንን  እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በተመሳሳይ ጊዜ እንዲያሰለጥኑ የፈቀደላቸው ፌደሬሽኑ ነው፡፡

ከመሰናበታቸው በፊት ያስመዘገቡት ውጤትም ያው ሀገር የሚያውቀው ነው፡፡ የስልጠና መንገዱም ቢሆን ከዓለም ፍጹም የራቀ  ስለመሆኑ ተጨባጭ ምክንያቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡

በኢትዮጵያ ለተጫዋቾች የሚሰጠው ስልጠና በቀን  ለምን ያህል ሰዓት?፣ ምን አይነት ስልጠና ይሰጣል?  ቢባል መልሱ  ለአጭር ስዓት መሀል በገባ ከመጫወት ያለፈ አይሆንም፡፡ ዓለም እያደገ ከመጣው ቴክኖሎጂ ጋር ራሱን ለማጣጣም የዘመነ ስልጠና በሚሰጥበት በዚህኛው ጊዜ የኢትዮጵያ እግር ኳስ የስልጠና መንገድ ግን አሁንም እዚያኛው ዘመን ላይ የቆመ መሆኑ በብዙ ዋጋ አስከፍሎታል፡፡

በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ 5 ጨዋታ በግብጽ 2 ለ 0 የተሸነፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ካደረጋቸው ያለፉት 30 የነጥብ ጨዋታች በ16ቱ ሲሸነፍ ማሸነፍ የቻለው በ4 አጋጣሚዎች ብቻ ነው፡፡

እንዲያው ለማሳያ ብሔራዊ ቡድኑን አነሳን እንጂ የኢትዮጵያ ክለቦችም የአፍሪካ መድረክ ተሳትፏቸው ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡

ለብሔራዊ ቡድኑ ውጤት ማጣት ቀጥተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋል ባይባልም እንኳን  ትንሽም ቢሆን እንደምክንያት የሚነሳው በሀገሪቱ አንድም የካፍን ዝቅተኛ የጥራት ደረጃ የሚያሟላ ስቴዲየም ባለመኖሩ  ጨዋታዎች ከሀገር ውጭ መደረጋቸው ሊሆን ይችላል፡፡ 

ግን ከሀገር ውጭ መጫወት  ለውድቀት ምክንያት እንደማይሆን ከጎረቤት ሀገር ሱዳን በላይ በቂ ማያሳየ የለም፡፡ በሀገሪቱ በተፈጠረው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት አይደለም ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ጨዋታዎች ይቅሩና የሊግ  ጨዋታዎቿን በታንዛንያ እና ሌሎች ሀገሮች የምታደርገው ሱዳን  እነዚህ ሁሉ ፈተናዎች ሳይበግሯት በቀጣይ ዓመት በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ መሆኗን አረጋግጣለች፡፡ ይሄ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ በተቸገረችበት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ምድቧን እየመራች ትገኛለች፡፡

ብቻ በተጫወተ ቁጥር የሚሸነፈው ብሔራዊ ቡድን  ሀገርን ለተጨማሪ ወጭ ከመዳረግ ያለፈ  አንዳች ነገር ማሳየት የማይችልበት ሁኔታ ላይ እንዳለ ከሚመዘገበው ውጤት በላይ ማሳያ ሊኖር አይችልም፡፡ 

ውጤቱ  ሲጠፋ  ጣት ከመጠቋቆም ውጭ ሃላፊነት ለመውሰድ ፈቃደኛ ያልሆኑ የእግር ኳስ ሰዎች የሞሉባት  ኢትዮጵያ ለባለ ዘርፈ ብዙው እና  ስር ለሰደደው የእግር ኳስ ህመሟ አሁንም  መፍትሄን ትሻለች፡፡

 በአንተነህ ሲሳይ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top