የኢትዮ - አሜሪካ ግንኙነት ከየት ወዴት?

6 Hrs Ago 231
የኢትዮ - አሜሪካ ግንኙነት ከየት ወዴት?

በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል ያለው ግንኙነት ረዥም ታሪክ አለው። ከ120 ዓመታት በላይ የተሻገረው ግንኙነታቸው ሀገራቱ ቅድሚያ በሚሰጧቸው ጉዳዮች ላይ ተመስርቶ እስከ አሁን ቆይቷል።

የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት የተጀመረው እ.አ.አ. በ1903 የአሜሪካ ተወካይ የሆኑት ሮበርት ስኪነር ከዳግማዊ አጼ ምንልክ ጋር የንግድ ስምምነት በፈረሙበት ወቅት እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡

ያኔ የተፈረመው የንግድ ስምምነት "የሁለቱን ሀገራት የወዳጅነት ግንኙነቱን ማስቀጠል እና ማጠናክር" የሚል መሪ ቃል የነበረው ሲሆን፣ ከስድስት ዓመታት በኋላም እ.አ.አ. በ1909 የአሜሪካን ሌጋሲዮን በአዲስ አበባ ተመስርቷል፡፡

በአምስት ዓመታቱ የጣሊያን ወረራ ወቅት አሜሪካ የጣሊያንን ወረራ ባትደግፍም በነበረው ሁኔታ ግን ሌጋሲዮኗን ዘግታ ነበር፡፡

በ1943 አሜሪካ ሌጋሲዮኗን እንደገና የከፈተች ሲሆን፣ ኢትዮጵያም በዚሁ ዓመት በአሜሪካ የኢትዮጵያ ሌጋሲዮን ከፍታለች፡፡ በ1949 ሌጋሲዮኖቹ ወደ ኤምባሲነት አድገዋል፡፡

በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ያደገ ሲሆን፣ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ወታደራዊ ድጋፍ ታቀርብ ነበር፡፡


ኢትዮጵያም በበኩሏ ለአሜሪካ አሥመራ ላይ የነበረውን ቀኛው ጣቢያ ለወታደራዊ መገናኛ እና ደኅንነት እንድትጠቀም የፈቀደችበት ጊዜ ነበር፡፡

የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሪቻርድ ኒክሰን "ኢትዮጵያ ከዩናይትድ ስቴትስ ታማኝ እና የማይለዋወጡ አጋር ሀገራት መካከል አንዷነች" ብለዋል፡፡

"የሰላም ጓድ (Peace Corps)" የተባለው በታዳጊ ሀገሮች ውስጥ በተለያዩ የልማት ሥራዎች ላይ ድጋፍ የሚያደርገው ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰማራው በኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን፣ ከአባላቱ መካከል በርካቶች ኢትዮጵያን ወድደው ቀሪ ዘመናቸውን እዚሁ ኖረዋል፡፡

ከ1966 ዓ.ም እስከ 1983 ዓ.ም ያለው ጊዜ በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረው ጠንካራ ግንኙነት የሻከረበት ወቅት ነበር፡፡

የደርግ መንግሥት ፊቱን ወደ ሶቪየት ሕብረት እና ሶሻሊዝም በማዞሩ የያኔዎቹ የአሜሪካ መሪዎች አኩርፈው ኢትዮጵያ ላይ ፊታቸውን አዙረዋል፡፡

ደርግ አሥመራ ላይ የነበረውን ቃኘው ጣቢያን ከአሜሪካ የቀማ ሲሆን፣ ይህ እርምጃ አሜሪካ የደርግን ሥርዓት ለማስወግድ እንድትወስን እንደገፋፋት በርካቶች ያወሳሉ፡፡

ደርግ ተወግዶ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ተሻሽሏል፡፡ አሜሪካ ጋር ትግል መግጠም ዋጋ እንደሚያስከፍል ከደርግ የተማረ የሚመስለው ኢሕአዴግ ካፒታሊዝምን እንደሚከተል በማወጅ ግንኙነቱን ቀጥሏል፡፡

በዚያ ወቅት የነበረው ግንኙነት አል-ሸባብን በጋራ በመዋጋት እና ከፍተኛ ሰብዓዊ ድጋፍን በመቀበል ይታወቃል፡፡ በርካታ የእርዳታ ድርጅቶችን በስሩ የያዘው የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID) ዋነኛው የኢትዮጵያ እርዳታ አቅራቢ ድርጅት እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

አሁን ያለው የሁለቱ ሀራት ግንኙነት ምን ይመስላል?

የሕግ መምህሩ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም 54 ዓመታት በአሜሪካ እንደኖሩ ይናገራሉ፡፡ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ የኢትዮጵያ እና አሜሪካን ግንኙነት በቅርበት ከሚከታተሉ ሰዎች ግንባር ቀደሙ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጋፉ ሕጎች ሲረቀቁ ከሴናተሮች ጋር ጭምር በመሟገትም ይታወቃሉ ፕሮፌሰሩ፡፡


ኢቢሲ ዶትስትሪም አሁን ስላለው የኢትዮጵያ እና አሜሪካ ግንኙነት የጠየቃቸው ፕሮፌሰር ዓለማየሁ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እጅጉን መሻሻሉን ተናግረዋል፡፡

ከለውጡ በፊት የነበረው የሀራቱ ግንኙነት በግለሰቦች እና ቡድኖች ተጠልፎ መርሕ አልባ ወደ መሆን ደርሶ እንደነበር የሚጠቅሱት ፕሮፌሰሩ፣ አሁን በተለይም ፕሬዚዳንት ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ እምርታ እያሳየ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

ለግንኙነቱ መሻሻል በርካታ ምሳሌዎችን አንስተው ከነዚህ ውስጥ ግን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር በነጩ ቤተ መንግሥት መገናኘታቸውን እንደ ዋነኛ ማሳያ ጠቅሰዋል፡፡

አንድ የውጭ ሀገር አምባሳደር የሥራ ደብዳቤውን ሲያቀርብ አልፎ አልፎ ፕሬዚዳንቶችን ሊያገኝ ይችላል ያሉት ምሁሩ፣ የአምባሳደር ብናልፍ ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር መገናኘት ግን ያልተለመደ እና በጣም ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን አውስተዋል፡፡

ከሙያ ልምዳቸው በመነሳትም የፕሬዚዳንት ትራምፕ እና አምባሳደር ብናልፍ ውይይት መልካም እንደነበረ ከፎቶዎቹ እና ከሁለቱ ሀገራት መግለጫዎች መረዳት ይቻል ብለዋል ፕሮፌሰር ዓለማየሁ፡፡

ሌላው የሁለቱ ሀገራት በዘላቂነት እየተሻሻለ መምጣት ማሳያው የአሜሪካ ማሪን ኮርፕስ ጄኔራል እና አፍሪኮም አዛዥ የሆኑት ጄነራል ማይክል ላንግሌይ የኢትዮጵያ ጉብኝት መሆኑን ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ተናግረዋል፡፡

የጄኔራሉ የኢትየጵያ ጉብኝት ሁለቱ ሀገራት በቀጣናው ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ያላቸውን ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፣ የአፍሪካ ቀንድንም ሆነ የአፍሪካን ሰላም ለማስጠበቅ ኢትዮጵያ ወሳኝ መሆኗን አውስተዋል፡፡

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ያስታወሱት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ፣ ውይይቱ ባለፉት አራት ዓመታት እንደተለመደው የአዛዥ እና ታዛዥ ሳይሆን የሀገራቱን ግንኙነት ማሻሻል ላይ እንዳተኮረ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መግለጫን ጠቅሰዋል፡፡

አሁን ያለው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በታሪክ ውስጥ እጅግ የተሻለ እንደሆነ ጠቅሰው ይህን ጅምር በጥንቃቄ መጠቀም እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡

ከዚህ በኋላ ያለው ግንኙነት በረጂ እና ተረጂ ስሜት ሳይሆን በልማት አጋርነት መሆን እንዳለበት የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ እንደሆነም ነው ፕሮፌሰር ዓለማየሁ የተናገሩት፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ "አሜሪካ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስትረዳ ነበር" ማለታቸውን አስመልክቶ አስተያየት የጠየቅናቸው ፕሮፌሰር ዓለማየሁ፣ ትኩረት መደረግ ያለበት በፕሬዚዳንቱ ንግግር ላይ ሳይሆን በፖሊሲ ደረጃ መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ለውጥ ላይ ነው ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ እየጠነከረች ስለሆነ የሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ ግንኙነትም እየተሻሻለ ወደ ላቀ ትብብር እንደሚያድግ ጠቅሰው፣ አሜሪካ ኢትዮጵያን የአፍሪካ መግቢያ በር አድርጋ ልትጠቀምባት እንደምትፈልግም ተናግረዋል፡፡

በአሜሪካ ያለው ዳያስፖራ ይህ መልካም ዕድል ወደ ላቀ ደረጃ እንዲያድግ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበትም ፕሮፌሰር ዓለማየሁ አሳስበዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ ሰሞኑን የአፍሪካ ቢሮ ከፍተኛ ኃላፊ አምባሳደር ትሮይ ፊተሬል፣ እንዲሁም የፕሬዝዳንት ትራምፕ የአፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ ከፍተኛ አማካሪ ማሳድ ቡሎስ ጋር መወያየታቸው የፕሮፌሰር ዓለማየሁን ሀሳብ የሚያጠናክር ነው፡፡

በለሚ ታደሰ

#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #America #Ethio_America_relationship


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top