የቀያይ ሰይጣናቱ ደስታ እና የአርሰናል መጥፎው ነሀሴ

8 Hrs Ago 69
የቀያይ ሰይጣናቱ ደስታ እና የአርሰናል መጥፎው ነሀሴ
2011/12 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የውድደር አመት 3ኛው ሳምንት መርሀ ግብር ማንችስተር ዩናይትድን ከአርሰናል አገናኝቷል፡፡
 
ይሄንን ቀን የአርሰናል ደጋፊዎች ፈጽሞ ሊያስታውሱት የማይፈልጉት እና አርሰን ቬንገር በድንጋጤ ወደ ገበያ የወጡበት ነው፡፡
 
ኢኮኖሚስቱ ሰው በአርሰናል በነበራቸው የ22 አመት ቆይታ ምን አልባትም ደካማ የሚባለው ስብስብ በዚያ የውድድር አመት ዩናይትድን የገጠሙበት ሳይሆን አይቀርም፡፡
 
ፈረንሳዊው አሰልጣኝ በወርሃ ነሃሴ ከማንችስተር ዩናይትድ ባደረጉት ጨዋታ በቅጣት እና በጉዳት እንዲሁም ከክለቡ የለቀቁትን እንደ ሴስክ ፋብሪጋስ እና ሳሚር ናስሪ አይነት ወሳኝ ተጫዋቾችን ሳይተኩ ለከባዱ ፍልሚያ መዘጋጀታቸው ዋጋ የከፈሉበት ነው፡፡
 
ዊሽኒ ሸዥኒ፣ ዦዋን ጅሩ፣ ካርል ጄኪንሰን፣ ሎረን ኮሽሊኒ፣ አርማድ ትራኦሬ፣ አሮን ራምሴ፣ ፍራንሲስ ኮክለን፣ ቶማስ ሮዝስኪ፣ ቲዮ ዋልኮት፣ ሮቢን ቫንፐርሲ እና አንድሬ አርሻቪን አሰልጣኙ በቋሚነት የተጠቀሟቸው ተጫዋቾች ናቸው፡፡
 
አንጋፋው አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ደግሞ አዲስ ፈራሚዎቹን ዲቪድ ዴሂያ፣ አሽሊ ያንግን እና ፊል ጆንስን ጨምሮ፣ ዋይኒ ሩኒ፣ ፓትሪክ ኤቭራ፣ ዳኒ ዌይልቤክ፣ ክሪስ ስሞሊንግ፣ ጆን ኢቫንስ፣ ናኒ፣ ቶም ክሌቨርሌይ እና ሊዩስ አንደርሰን በቋሚነት ተጠቅመዋል፡፡
 
በ2ሺዎቹ መጀመርያ በነበሯቸው ከዋክብት ከመልበሻ ክፍል እስከ ሜዳ ከተፎካካሪነት ከፍ ባለ ስሜት ለአመታት የዘለቁት ቡድኖች በ2011 ነሃሴ ወር በ3ኛ ሳምንት ኦልትራፎርድ ላይ ጨዋታቸውን ማድረግ ጀመሩ፡፡
 
75 ሺህ ተመልካቾች በታደሙበት የኦልትራፎርድ ጨዋታ ዩናይትድ 8 ለ 2 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸነፈ፡፡
 
ዋይኒ ሩኒ ሀትሪክ በሰራበት ጨዋታ፣ አሽሊ ያንግ ሁለት ግሩም ግቦችን አስቆጥሯል፡፡ ዳኒ ዌይልቤክ፣ ሊዩስ ናኒ እና ፓርክ ጄ ሱን ቀሪዎቹን ግቦች ከመረብ ያሳረፉ ናቸው፡፡
 
በሰሜን ለንደኑ ክለብ በኩል ካርል ጀኪንሰን 77ኛው ደቂቃ ላይ በቀይ ካርድ ከሜዳ በወጣበት ጨዋታ ሮበን ቫንፐርሲ እና ቲዮ ዋልኮት ሁለት ትርጉም አልባ ግቦች አስገኝተዋል፡፡
 
የመድፈኞቹ ተከላካዮች 90 ደቂቃ እንደ አንድ ቀን ረዝሞባቸው የዋና ዳኛው ሃዋርድ ዌብን ፊሽካ ሲጠብቁ ባመሹበት ጨዋታ አንገታቸውን ደፍተው ከኦልትራፎርድ ወጡ፡፡
 
አንዳች ትልቅ ማዕበል የወረደባቸው ቬንገር ከዚህ አስደንጋጭ ሽንፈት በኋላ ጊዜ ሳያባክኑ ወደ ገበያ በመውጣት የአሁንን የአርሰናል አሰልጣኝ ሚካኤል አርቴታ፣ ፐር መርቲሳከር፣ አንድሬ ሳንቶስ፣ ዮሲ ቤናዮን እና ፓርክ ቹ ያንግን አስፈረሙ፡፡
 
ሁለቱ ቡድኖች ከሁለት ወር በኋላ በሚጀምረው አዲሱ የውድድር አመት ከረጅም ጊዜ በኋላ በነሃሴ ወር ተገናኝተዋል፡፡
 
ለዚያውም በመጀመርያው ሳምንት እዚያው ኦልትራፎርድ ላይ፡፡ በእርግጥ አሁን ላይ በዩናይትድ እና አርሰናል መካከል ያለው ልዩነት ለንጽጽር የሚቀርብ አይደለም፡፡
 
ቀያይ ሰይጣናቱ በሊጉ ለመቆየት በተጫወቱበት አመት አርሰናል 2ኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅ ባለፉት 10 ግንኙነታቸውም መድፈኞቹ ፍጹም ብልጫ አላቸው፡፡ ይሄኛው ነሃሴስ?
 
በአንተነህ ሲሳይ

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top