በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት በፊት በተደረገ ጥናት ገንዘብ አውጥተው የዕድል ጨዋታ (ቤቲንግ) ከሚጫወቱ ዜጎች መካከል አብዛኛዎቹ ተማሪዎችና ሰራተኞች መሆናቸው ተረጋግጧል። መምህራን፣ የፋብሪካ ሰራተኞችና ሌሎችም ለዚህ አደጋ ከተጋለጡት መካከል ነበሩ።
ጥናት ከተደረገባቸው መካከል ደግሞ 26.4 በመቶ የሚሆኑት ምንም አይነት ስራ የሌላቸውና 24.1 በመቶዎቹ ደግሞ በቤቲንግ ሱስ የተጠመዱ ናቸው።
ከዚህ ቀደም ለኢቢሲ ሃሳብ የሰጡት የሥነ-ልቦና ባለሙያ አቶ ዳዊት ላቀው የስፖርት ውርርድ ቁማር ራስን እስከማጥፋት የሚያደርስ ሥነ-ልቦናዊ ጫናን እንደሚያስከትል መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
የብሔራዊ ሎተሪ አገልግሎት በማኔጅመንት ኢንስቲትዩት በኩል ያስጠናው ጥናትና በርካታ ወጣቶች በአቋማሪ ድርጅቶች በኩል ለከፍተኛ የማህበራዊ ችግር እየተጋለጡ መሆኑን ያመላክታል።
በዘንድሮው የበጀት ዓመት 11 ወራት ውስጥ ብቻ ዜጎች የውርርድ ሎተሪ ጨዋታዎችን ለመጫወት ከ16.6 ቢሊዮን በላይ ብር ወጪ ማድረጋቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።
የገቢዎች ሚኒስቴር ባወጣው የስፖርት ውርርድ ሎተሪ ፈቃድ አሰጣጥ መመሪያን ቁጥር 172/2013 መሰረት ደግሞ ማንኛውም 21 ዓመት ያሆነው ዜጋ በውርርድ ጨዋታዎች እንዳይሳተፍ ቢያግድም፤ ሕጉ ግን በተለያዩ ከተሞች ሲተገበር አይስተዋልም።
ከሰሞኑን በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት የዕድል ሎተሪ ፍቃድ አሰጣጥና ገቢ አሰባሰብን በተመለከተ የቀረበለት የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ውይይት አድርጓል።
በወቅቱ በቀረበው በፌዴራል ዋና ኦዲተር ሪፖርት በመሰረት በናሙና ከታዩ 80 የስፖርት ውርርድ አጫዋቾች መካከል 7ቱ በትምህርት ቤት እና በእምነት ተቋማት አካባቢ ቢሮ ከፍተው ሲሰሩ ተገኝተዋል።
በተጨማሪ 27ቱ ደግሞ ዕድሜያቸው ከ21 በታች የሆኑ ዜጎች ወደዕድል ጨዋታው እንዳይገቡ የሚያሳስብ ማሳሰቢያ ሳይለጥፉ ሲሰሩ እንደነበር ዋና ኦዲተር አመላክቷል።
ይሁንና ከአንድ ዓመት በፊት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ቤቲንግ ቤቶቹ በሕገወጥ ተግባራት በመሰማራታቸው፣ወጣቶችም 24 ሰዓት በቤቲንግ ቤቶች እየዋሉ በመሆኑና ተማሪዎችም ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዳይከታተሉ እንቅፋት ሆነዋል በሚል 3ሺ 241 የስፖርት አወራራጅ መደብሮችን ማሸጉ አይዘነጋም።
ቢሯቸው ቢዘጋባቸውም በርካቶቹ አሁንም የማቋመሩን ተግባር በኦንላይን እያቀረቡ መሆኑና በቤቲንግ ሱስ የተጠመዱበት ወጣቶች መኖራቸውን ኢቢሲ ዶትስትሪም በተለያዩ አካባቢዎች ባደረገው ማጣራት ማረጋገጥ ችሏል።
በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋና በኦሮሚያ፣ በትግራይና በአማራ ክልል አካባቢዎች የነበሩት የውርርድ ድርጅቶች በተለያየ ምክንያት መደብሮቻቸው ቢዘጉም በአሁኑ ወቅት በደቡብ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ቢሮ ከፍተው በስፋት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የገለጹት ደግም የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቤዛ ግርማ ናቸው።
ቁጥጥሩን በተመለከተ ገቢዎች ሚኒስቴር በደብዳቤ ሃላፊነቱን ወደአገልግሎቱ ማስተላለፉን አንስተው፤ ቁጥራቸው 174 የነበሩ የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶች ላይ በተደረገው ቁጥጥር አሁን ላይ ፍቃድ አውጥተው የሚሰሩት ወደ 94 መውረዳቸውንም አመላክተዋል።
ዘርፉ ክትትል እየተደረገበት ከተሰራበት ከፍተኛ ገቢ ማመንጨት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመው፤ በ11 ወራት ውስጥም ከአቋማሪ ድርጀቶች የተገኘው ገቢ 2.2 ቢሊዮን ብር መድረሱንም ነው ያስታወቁት።
የቋሚ ኮሚቴው አባላትም “ቤቲንግ ገንዘብ ስላስገኘ ብቻ መፈቀድ አለበት ወይ? ዜጎች ላይ የሚያደርሰው ማህበራዊ ቀውስ በአግባቡ ተጠንቶና ቁጥጥር ተደርጎበት መስራትስ አይገባም ወይ?” ሲሉ ከረር ያለ ጥያቄ አንስተዋል።
በኦንላይን በየደጁ የሚቀርበው የውርርድ ጨዋታ ላይም ልጆች ከ21 ዓመት በታች መሆናቸውን የሚለይበት የተረጋገጠ ማስረጃ ስለማይኖር አሁንም ጉዳዩ በጥናት ሊሰራበት እንደሚገባን አስረደተዋል።
የፌዴራል የሥነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ተወካይ በበኩላቸው ከአቋማሪ ድርጅቶቹ ጀርባ የውጭ ዜጎች መኖራቸውን አንስተው፤ ፈቃድ የሚያወጡት ግን ምንም ገንዘብ በሌላት ምስኪን ኢትዮያዊ ሴት አማካኝነት ነው ብለዋል።
ይህ አሰራር ከፍተኛ ገንዘብ ከሀገር እንዲሸሽ ስለሚያደርግ ካሁኑ መፈተሽ እንዳለበት አሳስበዋል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው የውርርድ ሱቆቹ ከሞራል አንጻር መዘጋታቸው አግባብ መሆኑን በግሌ አምንበታለሁ፤ ነገር ግን ሲዘጉ ከሎተሪ አገልግሎቱ ጋር በቅንጅት አለመሰራቱን አግባብ አልነበረም ብለዋል።
ምናልባትም ድርጅቶቹ ያልከፈሉት ቀሪ ዕዳ ቢኖርባቸው ለመለየት ከሎተሪ አገልግሎቱ ጋር በቅንጅት መስራት ይገባ እንደነበርም አስገንዝበዋል።
የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ አራሬ ሞሲሳ በበኩላቸው፤ ከውርርዱ የሚገኘው ብር ላይ ብቻ ሳይሆን ዜጎቻችን ላይ የሚደርሰው ተፅዕኖ ከግምት ያስገባ ቁጥጥር መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የአቋማሪ ድርጅቶቹን የቁጥጥር ስራ ማከናወን ያለበት ፈቀድ የሚሰጠው የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት በመሆኑ ከሕግ አንጻር ሃላፊነት የለኝም በሚል መሸሽ እንደማይገባ ነው የተናገሩት።
ከቁጥጥር ጋር ተያይዞ ያለውን የየሕግ ክፍተት በተመለከተ የገቢዎች ሚኒስቴርን ባካተተ መንገድ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲን፣ የፍትሕ ሚኒስቴርና የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ጉዳዩን ወስደው እስከመስከረም ወር ድረስ ችግሩን ሊፈቱ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በጌትነት ተስፋማርያም