"የተሻሻለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችን በወጀብ ውስጥ ባለው ዓለም ጠንካራ መሰረት ይዘን እንድንቆይ አስችሎናል" - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

6 Days Ago 334
"የተሻሻለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችን በወጀብ ውስጥ ባለው ዓለም ጠንካራ መሰረት ይዘን እንድንቆይ አስችሎናል" - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
"ጎረቤትን አስቀድሞ ወዳጅ እንዲያበዛ ተደርጎ የተቀረጸው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ ወጀብ በበዛበት ዓለም ውስጥ ፀንተን እንድንቀጥል አስችሎናል" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
 
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዓለም በጦርነት፣ በዋጋ ግሽበት፣ በታሪፍ ጦርነት፣ በብድር ጫና እና በበጀት ጉድለት በከፍተኛ መወናበድ ውስጥ እያለፈች መሆኑን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ኢትዮጵያ ይህን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ያስገባ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መቅረጽ ያስፈልጋት እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡
 
ቀድሞ በፖለቲካ፣ በሂደት እና በውክልና ላይ አተኩሮ የነበረውን እና ውጤት የማይመዘንበትን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ጎረቤት ላይ የሚያተኩር፣ ንግድ ወደሚያሰፋ እና ወዳጅ ወደሚያበራክት እንዲሁም ለብሔራዊ ጥቅም ቅድሚያ ወደ ሰጠ ፖሊሲ በመቀየሩ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡
 
እየተወናበደ ባለው ዓለም ውስጥ ገለልተኝነቱን ያልሳተ፣ አማራጭን ማበራከት፣ ገቢር ነበብ እና አጀንዳ ተቀባይ ብቻ ሳይሆን አጀንዳ ሰጪነት የአዲሱ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ምህዋሮች መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡
 
በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ማንም ላይ ተለጣፊ ሳትሆን፣ አማራጮችን አብዝታ ወዳጆችን በማፍራት፣ ወቅት በተቀያየረ ቁጥር የርዕዮተ ዓለም እስረኛ ሳትሆን ከአጀንዳ ተቀባይነት ወደ አጀንዳ ሰጪነት እየተሸጋገረች መሆኗን ጠቁመዋል፡፡
 
ኢትዮጵያ በመካከለኛው ምሥራቅ የምትከተለውን ግንኙነት እንደ ምሳሌ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ "ከዓረቦች ጋር ስለተወዳጀን እስራኤል አታስፈልገንም አንልም፤ በመካከላቸው ያለውን ቁርሾ ከቻልን መፍታት፣ ካልቻልን ግን ገለልተኝነታችንን ጠብቀን ከሁለቱም የምናገኘውን ጥቅማችንን እናስጠብቃለን" ብለዋል፡፡
 
ኢትዮጵያ ታሪካዊነቷን እና ታላቅነቷን በሚመጥን መልኩ በዓለም አቀፍ ደረጃም አጀንዳ ተቀባይ ብቻ ሳትሆን አጀንዳ ሰጪ ሆና መውጣት እንዳለባት ታምኖበት በዚሁ መንገድ ውጤታማ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
 
በዚህም ምክንያት በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ከኢትዮጵያ ጎን ሊቆሙ የሚችሉ ወዳጆችን ማፍራት መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡
 
በለሚ ታደሰ
 
 
 
 
 
 
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top