የእስራኤሉ “ዘመቻ ራይዚንግ ላየን” እና የኢራን ምላሽ

2 Days Ago 2905
የእስራኤሉ “ዘመቻ ራይዚንግ ላየን” እና የኢራን ምላሽ

የመካከለኛው ምስራቅ አሁንም እሳት እየዘነበበት ነው። አንዱ በአንዱ ላይ የመሳሪያ አይነቶችን ከመጠቀም ባለፈ የአጠፋሻለሁ አጠፋሃለው ዛቻውም ተባብሷል። በቀጣናው ሞት፣ አስከፊ ውድመትና የእናቶች ሰቆቃ የእለት ተዕለት አሳዛኝ ትዕይንት ሆኗል።

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ደግሞ ቀድሞውን ትርምስ በማያጣው አካባቢ ጠንካራ የደህንነት ስርዓት አላቸው የሚባሉት እስራአልና ኢራን ዳግም የጀመሩት ግጭት አካባቢውን ወደለየለት ጦርነት እንዳያመራው ተሰግቷል።

ቅድሚያ ጥቃቱን የጀመረችው እስራኤል ለሊቱን “ዘመቻ ራይዚንግ ላየን” (Operation Rising Lion) የተሰኘው የተቀናጀ ወታደራዊ ዘመቻ ከፍታለች።

ዘመቻ ራይዚንግ ላየን የእስራኤልን ህልውና ለማስጠበቅ የተካሄደ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሯ ቤንያሚን ኔታንያሁ  አስታውቀዋል።

የሞሳድ ደህንነቶች በኢራን ዋና ከተማ አቅራቢያ የድሮን ቤዝ ጭምር እስከመገንባት የደረሰ ለበርካታ ጊዜያት የፈጀ ዝግጅት ሲያደርጉበት የቆየ ዘመቻ መሆኑን ዘታይምስ ኦፍ እስራኤል አንድ የሀገሪቷን ባለስልጣን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።  

የጥቃቱ ዒላማ

ጎህ ከመቅደዱ በፊት 200 የእስራኤል ተዋጊ ጀቶች በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የኢራን ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን መሰንዘራቸውን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የኢራን የዩራኒየም ማብላያ ጣቢያዎች እና ሳይንቲስቶች እንዲሁም ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ላይ ባነጣጠረው የአየር ላይ ጥቃቶች ከሞት እስከ ከባድ ጉዳት መድረሱ በኢራን ባለስልጣናትም ጭምር ተረጋግጧል።

በጥቃቱ ዒላማ ከነበሩት መካከል የኢራን የዩራኒየም ማበልጸግያ ጣቢያው ናታንዝ አንዱ ነው።

የዓለም አቀፉ አቶሞክ ኢነርጂ ኤጀንሲ የናታንዝ ማብላያ ጣቢያ መመታቱን አስታውቆ፤ በአካባቢው የኑክሌር ጨረራዎች ጉዳት እንዳያስከትሉ ክትትል ሊደረግ እንደሚገባ አሳስቧል።

ናታንዝ ከምድር በላይና ከምድር በታች በተገነቡ ክፍሎች የኒኩለር ቦንብ ለመስራት የሚያገለግለው የዩራኒየም ማብላያ የሚከናወንበት ጥብቅ ስፍራ ነው። ምንም እንኳን ኢራን ማብላያው ለሰላማዊ አገልግሎት ነው የሚውለው ብትልም እስራኤል ግን ይህንን ፈፅሞ አትቀበለውም።

በተጨማሪ በቆም ከተማ አቅራቢያ በተራራ ስር የተገነባው ምስጢራዊው የፎርዶ የኑክሌር ጣቢያ፣ የኢራን ወሳኝ የሎጂስቲክስና የምርምር ማዕከል የሆነው የኢስፋሃን የኑክሌር ኮምፕሌክስ እንዲሁም ኢራን ፕሉቶኒየም እንድታመርት የሚያስችላት ኾንዳብ ጣቢያ በእስራኤል ጥቃት ደርሶባቸዋል።

እንዲሁም  በዋና ከተማዋ የሚገኘውና የወደፊት የኑክሌር ሳይንቲስቶች ማሰልጠኛዋ እና በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ዳርቻ ላይ የሚገኘውና በሩሲያውያን የተገነባው ለሰላማዊ አገልግሎት የሚውለው የቡሼህር የኑክሌር ኃይል ማመንጫ የጥቃቱ ዒላማ ከሆኑት መካከል ናቸው።

የኢራን ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ እንዳረጋገጠው፤ በጥቃቱ የኢራን አብዮታዊ ዘብ (IRGC) ዋና አዛዥ የሆኑት ሜጀር ጄኔራል ሆሴን ሳላሚ ተገድለዋል። ሟቹ ጄኔራል በቀጣናው በተካሄዱ ጦርነቶችና በኢራን ወታደራዊ እንቅሰቃሰሴዎችን በመቅረጽ ረገድ ቁልፍ ሚና እንደነበራቸው ይነገራል።

የኢራን ጦር ኤታማዦር ሹም ሜጀር ጀነራል መሀመድ ባገሪ፣ የኢራን የአቶሚክ ኢነርጂ ድርጅት የቀድሞ መሪ ፌሬይዶን አባሲ እና ቴህራን የሚገኘው ኢስላሚክ አዛድ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት መሀመድ መህዲ ቴህራቺ በዚህ ጥቃት መገደላቸው ተረጋግጧል።

ከእነዚህ ወታደራዊ መሪዎች የኑክሌር ተመራማሪዎች በተጨማሪ የካታም አል አንቢያ ማእከላዊ ዋና መስሪያ ቤት አዛዥ ጎላማሊ ራሺድ መገደላቸውን ኢራን አስታውቃለች።

የኢራኑ ታስኒም የዜና ወኪል በበኩሉ፤ እስራኤል ባደረሰችው የአየር ላይ ጥቃት የኑክሌር ሳይንቲስቶች ቁጥር ከስድስት ሊበልጥ እንደሚችል የሚጠቁሙ መረጃዎች እየወጡ ይገኛል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁኢራን ለእስራኤል ህልውና ስጋት መሆኗ እስኪቀለበስ ድረስ ዘመቻው ይቀጥላል” ማለታቸውን የሀገሪቷ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮዓቭ ጋላንት በበኩላቸው፤ ከተቀናጀው ዘመቻ በኋላ ኢራን በእስራኤል ላይ የድሮንና የሚሳኤል ጥቃት እንደምትፈጽም ይጠበቃል፤ ለዚህ ደግሞ ዝግጁ ነን ብለዋል።

የኢራን ምላሽ

ተሂራን የእስራኤል ጥቃት በአሜሪካ ድጋፍ የተፈጸመና ንጹሃን ላይ ያነጣጠረ ነው ስትል ገልጻለች። ኢራን በወታደራዊ ቃል አቀባይዋ በኩል ባስተላለፈችው መልክዕት በቴል-አቪቭ ላይ የከፋ አጸፋዊ እርምጃ እንደምስተወስድ ዝታለች።

በኋላም ተሂራን በ100 ድሮኖች የታገዘ ጥቃት በእስራኤል ላይ መፈጸሟን አልጃዚራና የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን አረጋግጠዋል።

በዚህም እስራኤል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጃለች። በአዋጁ መሰረት ማንም ሰው መንገድ ላይ እንዲወጣ እንደማይፈቀድለት ያመለክታል። ትምህርት ቤቶችን፣ ቢሮዎችን እና ሱፐርማርኬቶችን ጨምሮ ሁሉም የንግድ ተቋማት ተዘግተዋል።

የአየር ክልል በመዘጋቱና ጥቃት እንዳይደርስባቸው በመስጋት የእስራኤል መንገደኛ አውሮፕላኖች ከሀገሪቷ ውጪ በሚገኙ አየር ማረፊያዎች እንዲቆዩ ተደርጓል። 

ኢራን የላከቻቸውን ድሮኖች ለማስቆምም እስራኤል የአየር  ጥቃት መከላከያ ስርዓቷን እየተጠቀመች መሆኗን አስታውቃለች።

በሌላ በኩል እስራኤል በኢራን የፈጸመችውን ጥቃት ተከትሎ ኢራናውያን የተጠናከረ የአጸፋ እርምጃ እንዲወሰድ በሰላማዊ ሰልፍ ጠይቀዋል።

በተሂራን እንገላብ አደባባይ የወጡ ሰልፈኞች የሟች የጦር ሰራዊት አመራሮችን ፎቶ እና የኢራን ባንዲራ ይዘው ተቃውመቸውን አሰምተዋል።

የኢራን መንግስትም ሐገሪቷን መጠበቅ እንዳለበት የሚያሳስቡ መፈክሮች መሰማታቸውን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በጌትነት ተስፋማርያም


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top