እናት ልጇን ጎዳና ላይ ትታ እንድትሄድ የሚያደርጓት ገፊ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

2 Days Ago 315
እናት ልጇን ጎዳና ላይ ትታ እንድትሄድ የሚያደርጓት ገፊ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

 

በጅማ ከተማ ሰጦ በሚባል አካባቢ ነው፤ አንዲት ሴት በአካባቢው ስትጓዝ ያልጠበቀችውን ድምፅ ትሰማለች።

ወዲያውም ድምጽ ወደሰማችበት ጠጋ ብላ ስትመለከት ለዓይን የሚያሳሱ 2 መንታ ጨቅላ ሕፃናት ናቸው። በከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ሆና ነገሩን አጤነች።

ቅን አሳቢዋ ሴት ልጆቹን ጥላ ለመሄድ አልፈቀደችም፤  ይልቁንም ሕፃናቱን ከተተዉበት በማንሳት ለ"ሰው ለሰው የአረጋውያንና የህፃናት ማዕከል" ታስረክባለች።

የማዕከሉ መስራችና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ዘመናይ አስፋው፤ ቅን አሳቢዋ ሕጻናቱን አንስታ ባታመጣቸው ምናልባትም በአውሬ ይበሉ ይሆናል ሲሉ አስከፊውን ክስተት ያስረዳሉ።

ማህበሩ በዚህ መልኩ ጎዳና ላይ የተተው 155 ሕፃናት አንስቶ እያሳደገ መሆኑንም ነው ለኢቢሲ ዶትስትሪም የገለጹት። 

ኢቢሲ ዶትስትሪም ‘ወላጅ እናት በተፈጥሮ ከልጇ ጋር ያላትን ጥብቅ ቁርኝት እና ትስስር ተቋቁማ ልጇን ጎዳና ላይ ትታ እንድትሄድ የሚያደርጓት ገፊ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? ሲል  ጠይቋል።

ወ/ሮ ዘመናይ በምላሻቸው ሴቶች በቅርብ ዘመድ እንዲሁም ዘመድ ባልሆነ አካል በሚደርስባቸው ፆታዊ ጥቃት የተነሳ ልጅ ከወለዱ በኋላ አጋሮቻቸው ትተዋቸው ሊሄዱ እንደሚሄዱ ያስረዳሉ። 

በሌላ በኩል ቤተሰብ ባልፈቀደው የፍቅር ግንኙነት ውስጥ ሆነው ልጅ ሲወልዱ ጫናውን በመፍራት ልጃቸውን ትተው የሚሄዱ መኖራቸውንም ይገልጻሉ። 

ከዚህ ባለፈ ደግሞ  አብዛኛው ሰው ሕጻን ልጅ ያላትን ሴት ቀጥሮ የማሰራት ፍላጎት እንደሌለው አንስተዋል። እነዚህና መሰል ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ሴቶች ሕጻናትን በጎዳና እንዲጥሉ ምክንያት እነደሚሆንም አስረድተዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ህፃናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኮሙኒኬሽን  ዳይሬክተር የሆኑት ሀዲጎ ፀሐዬ በበኩላቸው፤ በጉዳዩ ላይ የአመለካከት ችግር መኖሩን ይገልፃሉ።

እናቶች ልጆቻቸውን ትተው እንዲሄዱ ከሚያደርጋቸው ድርጊት አንዱ የፆታዊ ጥቃት የሚያደርስባቸው ተጽእኖ መሆን ጠቁመዋል።

የኢኮኖሚ ጫና ብሎም ልጅ የፈጣሪ ፀጋ ነው ብሎ ካለማመን በሚመነጭ ሁኔታ የምፈልገውን ፆታ አልወለድኩም በሚል ምክንያት ጭምር ይህን ድርጊት እንደሚፈፅሙ መኖራቸውንም ያነሳሉ። 

በዚህ መልኩ በወላጆቻቸው የተተዉ 220 ህፃናት በክበበ ፀሐይ የሕፃናት መርጃ ማዕከል ውስጥ እንደሚገኙና ሌሎች በርካቶች ደግሞ በተለያዩ ማዕከላትና በግለሰቦች በኩል እንክብካቤ እያገኙ መሆኑን ይገልጻሉ።

ሕፃናትን በጎዳና ትቶ መሄድ ከሚያስከትለው ማህበራዊ ቀውስ ባሻገር ሕፃናቱ ለአዕምሮ እድገት መቀነስ እና ለሌሎችም በሽታዎች እንሚያጋልጣቸውን ነው ያስረዱት።

ያለውንን የአመለካከት ክፍተት ለመሙላት ግንዛቤ የማስጨበጥ፣ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ለችግሩ ተጋላጭ የሆኑ ህፃናትን እንክብካቤ እንዲያገኙ ለማድረግ  እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በአፎሚያ ክበበው

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top