የዘምዘም ውኃ የፈለቀላት የታዛዥነት እና የጥንካሬ ምልክቷ ሀጀር

1 Day Ago 804
የዘምዘም ውኃ የፈለቀላት የታዛዥነት እና የጥንካሬ ምልክቷ ሀጀር

ሀጀር የነቢዩላሂ ኢብራሂም ባለቤት የሳራ አገልጋይ ነበረች። ሳራ መሃን (መውለድ የማትችል) ስለነበረች ነቢዩላሂ ኢብራሂም (ዓ.ሰ) ሀጀርን እንዲያገቧት እና በእርጅና ዘመናቸውም ቢሆን የሚናፍቁትን ልጅ እንዲያገኙ ጠይቀቻቸው።

ነቢዩላሂ ኢብራሂምም ፈቃደኛ ሆነው ሀጀርን አገቧት፤ ኢስማኤል የተባለ ልጅም ተወለደ።

ሀጀር የሚያምር እና እጅግ የሚያሳሳ ልጅ በመውለዷ ሳራ በቅናት መንፈስ የተነሣ ከሀጀር ጋር አንድ ላይ መኖር ፈፅሞ እንደማትችል ገለጸች፤ አቋሟንም በመሐላ አጠናከረች።

ነቢዩላሂ ኢብራሂምም (ዓ.ሰ) ይህንኑ ስላወቁ ሀጀርን ይዘው ወደ መካ በረሃ ተሰደዱ።

ከግብጽ ደቡባዊ አቅጣጫ ተነሥተው እጅግ አድካሚ እና አሰልቺ የሆነ እና ብዙ ቀናትን የፈጀ ጉዞ ወደ መካ በረሃ አደረጉ።

ነቢዩላሂ ኢብራሂም (ዓ.ሰ) ከመካ በረሃም ደረሱ። መካ በወቅቱ እንኳን የሰው ዘር ወፍ እንኳን ዝር የማይልበት ምድረ በዳ፣ አልፎ አልፎ አርብቶ አደሮች ለእንስሶቻቸው የሚጋጥ ነገር ፍለጋ የሚያልፉበት ጭው ያለ ስፍራ ነበር።

ይህ ስፍራ አላህ በብቸኝነት የሚመለክበት ስፍራም እንደነበረ የተሰነዱ ኪታቦች ይመሰክራሉ።

ነቢዩላሂ ኢብራሂም በመካ በረሃ ከሀጀር እና ኢስማኤል ጋር አብረው ከቆዩ በኋላ በጊዜ ሂደት ከአነስተኛ ምግብ እና ውኃ ጋር ጭር ባለው በረሃ ላይ አስቀምጠዋቸው መመለስ ጀመሩ።

ሀጀር በዚህ ወቅት በፍጥነት ከፊት ለፊታቸው በመቆም “የት ነው የምትሄደው? እዚህ ጭር ያለ ምድረ በዳ ላይ ጥለኸን ልትሄድ ነው?” በማለት ጠየቀቻቸው። ኢብራሂምም (ዓ.ሰ) መልስ ሳይሰጧት ጉዞአቸውን ቀጠሉ።

ሀጀርም በመከተል ጥያቄዋን በተደጋጋሚ መጠየቅ ጀመረች፤ ነገር ግን መልስ ልታገኝ አልቻለችም። በመጨረሻም ‘ከአላህ ታዝዘው ይሆናል’ በማለት አሰበች፣ ይህንንም ለማረጋገጥ “እዚህ እንድትተወን ያዘዘህ አላህ ነውን?” በማለት ጥያቄ አቀረበችላቸው። እርሳቸውም “አዎ አላህ ነው” በማለት መልስ ሰጧት።

ከዚያም ሀጀር፣ “ትዕዛዙ ከአላህ ከሆነማ መሄድ ትችላለህ፣ እርሱ ፈፅሞ እንድንጠፋ አያደርገንም” በማለት ቢሄዱ ፍቃደኛ መሆኗን ገለጸችላቸው።

ነቢዩላሂ ኢብራሂም (ዓ.ሰ) ከልጃቸው እና ከሀጀር ዕይታ የሚሰውራቸው ተራራ እስኪያገኙ ድረስ ረጅም ርቀት ተጓዙ፤ በተራራውም በማረፍ እጆቻቸውን ወደ ሰማይ በመዘርጋት፣ “ጌታችን ሆይ! እኔ አዝመራ በሌለው ሸለቆ ውስጥ በተከበረው ቤትህ (ከዓባ) አጠገብ ከዘሮቼ አስቀመጥኩኝ፤ ሰላትን ያቋቁሙ ዘንድ አስቀመጥኳቸው፣ ከሰዎች ልቦች ወደ እነርሱ የሚናፍቅ አድርግ። ያመሰግኑህም ዘንድ ከፍሬዎች ስጣቸው” ብለው አላህን ተመጻኑ።

ነቢዩላሂ ኢብራሂም ወደ ሀገራቸው በመመለስ ሕዝባቸውን ወደ አላህ መጣራት ጀመሩ። ሀጀር ግን ልጇን እያጠባች ስለነበር የውኃ ጥሙን መቋቋም አቃታት።

ነቢዩላሂ ኢብራሂም ከስልቻው የተውላቸው ጥቂት መብል እና ውኃ ከጥቂት ቀናት በኋላ አለቀባቸው፤ ሕፃኑ ኢስማኤልም የበረሃ ንዳዱን መቋቋም አቅቶት እያለቀሰ ያስቸግራታል።

ሀጀር ልጇን ኢስማኤልን አስቀምጣው ጥሟን ለማስታገስ፣ ልጇን ለማጥባት የሚያስችላትን ነገር ለማግኘት ከ‘ሰፋ’ እና ‘መረዋ’ ተራሮች መካከል ወዲህ እና ወዲያ መሯሯጥ ጀመረች። ወደ ላይ ብታይ፣ ወደ ሸለቆው ብትወርድ የሚላስ የሚቀመስ ግን ማግኘት አልቻለችም።

ሀጀርም ለሰባት ጊዜ በሁለቱ ኮረብታዎች ከተመላለሰች በኋላ በእጅጉ ደክማ እና ዝላ የምታደርገው ነገር በማጣቷ በእጅጉ አዝና ወደ ልጇ ኢስማኢል ትመለሳለች።

በዚህ ጊዜ ታዲያ በአላህ ተዓምር ከልጇ እግር ሥር ታላቅ የሆነ ምንጭ ፈልቆ አስተዋለች።

ያንን ውኃ እንዳገኙ ሕይወታቸው ላይ ትልቅ ለውጥ ታየ፤ ‘ዘምዘም’ የተባለው ወኃ ፈለቀላት። ይሄን ውኃ ከየመን ወደ ሻም ለሚዘልቁ የሲራራ ነጋዴዎች እየሸጠች ከሚበላ እና ከሚጠጣ እየለወጠች እራሷንም ሆነ የልጇን ሕይወት ማቆየት ቻለች።

ጭው ካለው የመካ በረሃ የተፈጠረ ታሪክ ነው። በዚያ ዘመን ለነበሩ የሰው ልጆች የመኖርን ኅልውና የሚፈታተን፣ በትዕግሥት፣ ሩቅ በማሰብ፣ በፈጣሪ እዝነት እና ቸርነት እንጂ ሰዎች ሕይወታቸውን ለማቆየት የሚቸገሩበት እጅግ አደጋች የሆነ ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ ነው።

የነቢዩላሂ ኢብራሂም ልጅ የሆነው የኢስማኤል እናት ሀጀር በመካ በረሃ ከነልጇ ፈተናውን ለመጋፈጥ የወሰነችበት፣ ከፈጣሪ ዘንድ ብርታት እና ጥንካሬን ያገኘችበት፣ የባለቤቷን ትዕዛዝ ያከበረችበት፣ ይሁንታን የተላበሰ በብዙዎች ዘንድ ዛሬም ድረስ የሚወሳ ምርጥ ስብዕና ነው።

ዛሬ ላይ ከመላው ዓለም ለሀጅ ጉዞ የሚያደርጉ ሙስሊም ምዕመናን ‘ዘምዘም’ ውኃን ቀምሰው ለዘመድ አዝማድ ሳይዙ አይመለሱም።

የሀጀርን እግር ተከትለው በሰፋ እና መረዋ መካከል 7 ጊዜ በመመላለስ ሀይማኖታዊ ሥርዓቱን ይከውናሉ፤ ዱዓና ጸሎት ያደርሳሉ።

በመሐመድ ፊጣሞ

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top