ከመላው ዓለም የተውጣጡ ሙስሊሞች የህይወት ዘመናቸው ህልም የሆነውን ሀጅ ለመፈፀም ለቀናት የሚቆዩባት፣ እስላማዊ ወንድማማችነት እና አንድነት በተግባር የሚታይባት ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ ቅዱስ ስፍራ ናት።
አቅሙ ያለው ጤናማ የሆነ ማንኛውም ሙስሊም በህይወት ዘመኑ አንድ ጊዜ ወደ ሳዑዲ አረቢያ በማቅናት ሀጅ ማድረግ ኢስላማዊ ግዴታው ነው።
ከ5ቱ የእስልምና መሰረቶች አንዱ የሆነውን ሀጅ ለመፈፀም ወደ መካ የሚጓዙ ሙስሊሞችን ተቀብላ የምታስተናግደው የዓለማችን ትልቋ የድንኳን ከተማ ሚና በርካታ መገለጫዎች አሏት።
ከተማዋ 2.5 ሚሊዮን ስኩዌር ሜትር ስፋት ያላት ሲሆን ከመካ በስተ ምስራቅ 6 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በመካና በአራፋት ተራራ መካከል በሚገኝ ሜዳማ ስፍራ ውስጥ ትገኛለች። ይህም ከሃረም መስጂድ ከ5 እስከ 6 ኪሎ ሜትር ትርቃለች፡፡
በአንድ ጊዜ 3 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን መያዝ የሚችል፣ ዘመናዊ ማቀዝቀዥ የተገጠመላቸው ከ100 ሺህ በላይ ዘመናዊ ድንኳኖች አሏት። የሀጃጆች ጊዜያዊ ማረፊያ እና የሀጅ ሥነ-ስርዓት መከወኛ ቅዱስ ስፍራዎች መካከል ተጠቃሽ አድርጓታል።
ይህንን ጊዜያዊ ከተማ ለተመለከተ በተለይም ከላይ ሲመለከቱት የድንኳኖቹ ነጭ ቀለም ትኩረትን ይስባል። የድንኳኖቹ ወጥ የሆነ ቀለም ብቻ ሳይሆን፣ አብዛኛውን ጊዜ ሀጃጆች ቀላል ነጭ ልብሶችን (ለወንዶች ኢህራም) ይለብሳሉ፣ ይህም የዘር ወይም ማህበራዊ ልዩነት ሳይኖር የእስልምናን እኩልነት እና አንድነት የሚያጎላ ነው።
ድንኳኑ እሳት መቋቋም ከሚችል ፋይበር ግላስ የተሰራ ሲሆን በውስጥና በአካባቢው የሀጃጆችን ምቾትና ደህንነት ለመጠበቅ የማረፊያ፣ የሞግብ ማቅረቢያ፣ የህክምና፣ የኤሌክትሪክ እና የኢንተርኔት አቅርቦቶች አሉት።
ሀጃጆች በድንኳን በሚኖራቸው ቆይታ የጋራ መጠቀሚያ ስፍራዎች፣ ሻወር ቤት፣ ሽንት ቤት፣ ኡዱዕ ማድረጊያና መስገጃ ቦታዎች ተዘጋጅተዋል።
በእያንዳንዱ ድንኳን ውስጥ የሙቀት መጠን ከሚገባው በላይ ከጨመረም ሆነ የእሳት አደጋ ቢነሳ ዘመናዊ የደህንነት መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂ ተገጥሞለታል።
የሙቀት መጠኑ በሚጨምርበት ወቅት በድንኳኑ የተገጠው ቴክኖሎጁ ወዲያው ውሃ በመርጫት ማቀዝቀዝ ይችላል። በሚና የሀጅ ተጓዦች የጤና እክል ሲገጥማቸው አስፋላጊውን የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ ከ550 በላይ አልጋ ያላቸው አራት ሆስፒታሎች፤ 26 መካከለኛ የህክምና መስጫ ማዕከላት ለ24 ሰዓት አገልግሎት ይሰጣሉ።
ታካሚዎችን ለማጓጓዝም 100 አነስተኛ እና ከ75 በላይ ትላልቅ የአምቡላንስ መኪናዎች በተጠንቀቅ ላይ ናቸው። የሀጃጆችን ምቾት ለመጠበቅም ዘመናዊ የትራንስፖርት እና ዘመናዊ የቆሻሻ ማስወገጃ ስርዓት ተሰርቷል። በየዓመቱ 2 ሺህ 200 በላይ በጎ ፈቃደኞች ለሀጃጆች መረጃ በመስጠትና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ይሳተፋሉ።
ሀጃጆች በሚና የሚያሳልፉት ሶስት ቀናት የተባረኩ ቀናት ናቸው፤ በዚህ ወቅት የአላህን ትዕዛዝ በመፈጸም መስዋዕት ያቀርባሉ፣ ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ፣ ምህረትን እና ይቅርታን ይለምናሉ።
ዓመቱን በሙሉ ሰው አልባ ሆና የምትከርመው ሚና በሀጅ ወቅት የእንግዶቿን ምቾትና ደህንነት ጠብቃ ጥራት ያለው አገልግሎት የምትሰጥ የዓለማችን ትልቋ የድንኳን ከተማ ያደርጋታል።
ነጭ ድንኳኖች እንደ ተቀራረቡ አማኝ ልቦች መስመራቸውን ይዘው ፣ በሰይጣን ማታለያ ሀሳብ ሳይበርዙ በፀና አቋምና ንፁህ ህሊና ለሰዎች ሁሉ የምታንጽ ጊዜያዊ ከተማ ትመስላለች ሚና የዓለማችን ትልቋ የድንኳን ከተማ።