የተመድ ፀጥታ ምክር ቤት የደቡብ ሱዳንን የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በአንድ ዓመት እንዲራዘም ውሳኔ አሳልፏል፡፡
የሰላም ማስከበር ተልዕኮው እ.አ.አ እስከ ሚያዚያ 30 ቀን 2026 ድረስ እንዲራዘም በ12 የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ድምጽ ተወስኗል።
በአሜሪካ የተዘጋጀው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ሀሳብ በተለያዩ ምክንያቶች የዘገየ ሲሆን፣ በመጨረሻም ሰፊ ውይይት ከተደረገበት በኋላ በድምጽ ብልጫ ጸድቋል።
የሰላም አስከባሪ ኃይሉ የሰላማዊ ሰዎች ጥበቃን፣ የእርዳታ አቅርቦትን መደገፍን፣ የ2018 የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት ማረጋገጥን፣ የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰትን መመርመርን ጨምሮ ኃላፊነቱን ተግባራዊ ለማድረግ "አስፈላጊውን ዘዴ ሁሉ እንዲጠቀም" የተፈቀደለት መሆኑን ከተመድ ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
አሥራ አምስት አባላት ባሉት ምክር ቤት ሩሲያ፣ ቻይና እና ፓኪስታን በሂደቱ ላይ ያላቸውን ቅሬታ አቅርበው ድምጸ ተአቅቦ አድርገዋል፡፡
ሩስያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮውን እንደምትደግፍ ጠቅሳ፣ አሜሪካ ግን በደቡብ ሱዳን መንግሥት ላይ ጫና እያደረገች ነው ስትል ከስሳለች።
በተመሳሳይ ቻይና የተልዕኮው መራዘም በመሬት ላይ ያለውን እውነታ የማያንጸባርቅ እና ከልክ ያለፈ ግፊት እንደሚፈጥር መጥቀሷን ስፑቲኒክ ዘግቧል።
በለሚ ታደሰ