በ48 ደቂቃ 40 ሚሊዮን ፓውንድ የወጣበት የዓለም ውዱ ተጫዋች

7 Hrs Ago 72
በ48 ደቂቃ 40 ሚሊዮን ፓውንድ የወጣበት የዓለም ውዱ ተጫዋች
ፍርድ ቤት ዝነኛ ያደረገው የዓለም ውዱ እግር ኳስ ተጫዋች ወይም ባለቤት አልባው የዓለም ውዱ ተጫዋች አየተባለ ይጠራል::
እንደ ኔይማር ኬይሊያን ምባፔ ፍሊፔ ኩቲኒሆ እና ጃኦ ፍሊክስ አይነት የእግር ከዋክብት ከ100 ሚሊየን ፓውንድ በላይ ወጥቶባቸው ተዘዋውረው ይሆናል። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ የአለማችን ውድ ተጫዋቾች አይደሉም። የአለም ውዱ ተጫዋች ሜዳ ውስጥ ለቆየበት 48 ደቂቃ ብቻ 40 ሚሊየን ፓውንድ የወጣበት ዣን ኬቪን ኦገስቲን ነው።
 
ለዚህ ታሪካዊ ተጫዋች በ1 ሰከንድ 13 ሺ ፓውንድ የከፈለው ደግሞ ሀብታሙ ሪያል ማድሪድ ወይንም በቅርብ አመታት የአለም እግር ኳስ የገንዘብ አወጣጥ ሚዛን የቀየሩት የአረብ ክለቦች ሳይሆኑ ለዝውውር በታሪኩ ከ30 ሚሊየን ፓውንድ በላይ አውጥቶ የማያውቀው ሊድስ ዩናይትድ ነው ቢባል ማን ያምናል።
በታዳጊነታቸው የአለምን እግር ኳስ ይቆጣጠራሉ ተብለው በብዙ ተስፋ ከተጣለባቸው ነገር ግን የታሰበው ቦታ ሳይደርሱ ከቀሩት በርካታ ተጫዋቾች ይሄ ፈረንሳዊ አጥቂ አንደኛው ነው።
 
ከፒኤስጂ አካዳሚ የተገኝው ዣን ኬቪን ኦገስቲን ዝላታን ኢብራሂሞቪችን ጨምሮ ብዙ የአጥቂ አማራጮች ያለው ቡድን ውስጥ በሚፈልገው ልክ የመሰለፍ ዕድል በማጣቱ በ13 ሚሊየን ፓውንድ አር ቢ ላይብዚንግን ተቀለቃለ።
 
በላይብዚንግ ከቲሞ ቨርነር እና ዩሱፍ ፖልሰን በመፎካከር የቋሚነት ቦታውን ለማስጠበቅ ቢሞክርም በሚጠበቀው ልክ ያልሆነው ኦግስቲን ህይዎት በጀርመን ከባድ ሆነበት።
 
በመቀጠል በውሰት ወደ ሀገሩ ሞናኮ ቢያመራም በጥቂት ጨዋታዎች ላይ ከመሰለፍ ያለፈ ነገር ሳይፈጥር እንዲመለስ ሆነ።
 
በአውሮፓ የተጫዋቾች ዝውውር ከተፈጸሙ አስገራሚም ሁነቶች አንደኛው የተፈጸመው እዚህ ጋር ነው።
 
በውቅቱ በሻምፒዮን ሽፑ ይሳተፍ የነበረው ሊድስ ዩናይትድ ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማደግ የጀመርውን ግስጋሴ ለማሳካት ፈረንሳዊውን አጥቂ በውሰት የግሉ አደረገ።
 
የውሰት ውሉ ስምምነት ለ6 ወር የሚቆይ ሲሆን ክለቡ ወደ ሊጉ ካደገ ግን ተጨዋቹን በ18 ሚሊየን ፓውንድ ለአምስት አመት በሚቆይ ውል በቋሚነት የግሉ እንደሚያደርግ በስምምነቱ አስቀምጧል።
 
ምንም እንኳን በማርሴሎ ቤልሳ የሚሰለጥነው ሊድስ ከተጫዋቹ የሚፈልገውን ግልጋሎት ባያገኝም ከ16 አመት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ተመለሰ።
 
የወቅቱ የሊድስ አሰልጣኝ ማርሴሎ ቤልሳ በ3 ጨዋታዎች የፓትሪክ ባምፎርድ ተቀያሪ አድርገው ለ48 ደቂቃዎች ብቻ ዕድል የሰጡት አጥቂ ወደ መጣበት ክለብ እንዲመለስ አዘዙ።
 
ላይብዚን ግን ተጫዋቹን ሳይሆን በስምምነቱ የተጠቀሰውን 18 ሚሊየን ፓወንድ እንዲሰጠው ጠየቀ። የተጫዋቹ የውሰት ውል የሚጠናቀቀው እስከ ሰኔ 30 ፡ 2020 ቢሆንም በወቅቱ በተከሰተው የኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ጨዋታዎቹ ተገፍተው እስከ ሀምሌ በመድረሳቸው ተጫዋቹን ያልፈለገው ሊድስ በዚህ አመክንዮ ገንዘቡን እንደማይከፍል ይፋ አደረገ።
 
አር ቢ ላይብዚንግም ጉዳዮን ወደ ፊፋ ወሰደው ፊፋም ሊድስ ዪናይትድ ተጫዋቹን የማስፈረም እና ገንዘቡንም የመክፈል ግዴታ እንዳለበት ውሳኔ አሳለፈ።
 
በዚህ ሂደት በሁለቱም ክለቦች ያልተፈለገው እና ባለቤት አልባው ዦን ኬቨን ኦጉስቲን ካለማንም ፈቃድ ወደ ፈረንሳይ ተመልሶ ለኖንት ፊርማውን አስቀመጠ።
 
የፊፋ ውሳኔ ያልተዋጠለት ሊድስ ለአለም አቀፉ ስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት (ካስ) ይግባኝ ቢልም ተቋሙ የመጀመርያውን ውሳኔ አጸና።
 
ሊድስ በመጠነኛ ድርድር አር ቢ ላይብዚንግ 2.5 ሚሊየን ፓውንድ እንዲቀንስለት አድርጎ 15.5 ሚሊየን ፓውንዱን ከፈለ።
 
ነገሩ በዚህ አላበቃም የፊፋን ውሳኔ የሰማው ኦግስቲን አጋጣሚውን ተጠቅሞ በሊድስ ላይ ሌላ ክስ መሰረተ።
 
የእነሱ ተጫዋች መሆኔን ካመኑ ደመወዜን ሊሰጡኝ ይገባል በማለት አቤቱታውን አቀረበ። ፊፋም ተጫዋቹ የጠየቀው የ5 አመት ደመወዙን 24.5 ሚሊየን ፓውንድ እንዲከፈለው ወሰነለት።
 
አንዱን የፍርድ ሂደት ተወጣሁ ሲል ሌላ የከበደ ጉዳይ የተተካለት ሊድስ ዩናይትድ ጉዳዩን ይግባኝ ቢልም የተለየ ውሳኔ ማግኝት አልቻለም።
 
ሊድስ ዩናይትድ 90 ደቂቃ እንኳን ላላገለገለው እና አንዳች ነገር ላልፈጠረው ተጫዋች በሳምንት 93 ሺህ ፓውንድና የፊርማ 2.5 ሚሊየን ፓውንድ ጉርሻ እንዲከፍል የተገደደበት አጥቂ ዦን ኬቨን ኦግስቲን ይህ ታሪክ ተመዝግቦለታል፡፡
 
28 አመቱ ላይ የደረሰው ይህ አጥቂ በአሁን ሰዓት ለፖላንዱ ክለብ ሞተር ሉቢን እየተጫወተም ይገኛል፡፡
 
በአንተነህ ሲሳይ

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top