ከሽያጭ ሰራተኞች እስከ ጸጉር አስተካካዮች የኦክላንድ ሲቲ ተጫዋቾች:- ከ10 ለ 0 ሽንፈት ጀርባ አስደናቂው የኦክላንድ ሲቲ ተጫዋቾች ታሪክ

1 Day Ago 1529
ከሽያጭ ሰራተኞች እስከ ጸጉር አስተካካዮች የኦክላንድ ሲቲ ተጫዋቾች:- ከ10 ለ 0 ሽንፈት ጀርባ አስደናቂው የኦክላንድ ሲቲ ተጫዋቾች ታሪክ

ፊፋ በአዲስ የውድድር ቅርጽ ማካሄድ በጀመረው የክለቦች አለም ዋንጫ ለመጀመርያ ጊዜ 32 ክለቦች ተሳታፊ ሆነዋል። በምድብ 3 ከባየር ሙኒክ፣ ቤኔፊካ እና ቦካጁኒየርስ የተደለደለው ኦክላንድ ሲቲ አንዱ ነው።

የኒውዝላንዱ ተወካይ በመጀመርያ ጨዋተው በሙኒክ 10 ለ 0 ተሸንፏል። የሚገርመው የኦክላንድ ሲቲ  ተጫዋቾች መደበኛ ሙያቸው እግር ኳስ  አለመሆኑ ግርምትን ፈጥሯል።

10 ግብ የተቆጠረበት ኮኖር ትሬሲ የተባለው ግብ ጠባቂ በኒውዝላንድ በሚገኝ የፋርማሲ ድርጅት ውስጥ  የሚሰራ ነው።  የ28 አመቱ ትሬሲ ጨዋታው ወደ ሚደረግበት አሜሪካ ለመጓዝ  የጉዞ ገንዘብ ለማሰባሰብ ብዙ ፈተና ማለፉን ተናግሯል።

ከሚሰራበት ድርጅት የአመት እረፍቱን ተጠቅሞ የወጣው ግብ ጠባቂ አለም ላይ አሉ ከሚባሉ ትልልቅ ክለቦች ጋር የመጫዎት ዕድሉን ለመጠቀም ብዙ ዋጋ መክፈሉን አሳውቋል።

በጨዋታው ምንም እንኳን 10 ግብ ቢቆጠርበትም የአለም ምርጡ ግብ ጠባቂ ከሆነው ማኑኤል ኑየር ጋር የመገናኝት ህልሙን ማሳካቱ ግን ሁሉንም ድካም እንደሚያስረሳው ገልጿል።

አጥቂው አንጉስ ኪልኮሊ በአንድ የቁሳቁስ መሸጫ ውስጥ ስራ አስኪያጅ ሆኖ የሚሰራ ነው። የ29 አመቱ ተጫዋች እና የሽያጭ ሰራተኛ ሲናገር በአሜሪካ ቆይታው የሚከፈለው ነገር እንደሌለ እና ብዙ ጓደኞቹ በገንዘብ ዕጥረት ምክንያት መቅረታቸውን ይፋ ማድረጉ አነጋጋሪ ሆኗል።

ሌላኛው አስገራሚ ነገር ለአሜሪካ ጉዞ እያንዳንዳቸው የሚያወጡት ገንዘብ ከአመታዊ ደመወዛቸው በሁለት እጥፍ የበለጠ መሆኑ ነው።

ለእግር ኳስ የተለየ ፍቅር ያለው ሌላኛው ዲን ሀየር የተባለው የመሀል ተከላካይ አባት እና እናቱ የ12  አመት ልጅ እያለ በመለያየታቸው ብዙ ዋጋ እንደከፈለ ይናገራል።

በነበረው ድንቅ ችሎታ በጃፓን ሊግ የመጫዎት እድል ቢያገኝም ቋንቋውን እና ባህሉን ባለመልመዱ ወደ ኒውዝላንድ መመለሱን አስታውሷል። በሀገሩ ግን የሚወደውን እግር ኳስ ለመጫዎት ምቹ ባለመሆኑ ይቆጫል።

በኒውዝላንድ እግር ኳስ ተጫዋች ከመሆን ይልቅ  የልብ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት መሆን ይቀላል በማለት በምሬት በዚያች ሀገር ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ምንም እንዳልሆነ ተናግሯል።

ይሄን የሚለው ተጫዋች በሀገሩ ዲኤኤስ በተባለ ኩባንያ ውስጥ የጌጣጌጥ ዛፎችን በመሸጥ የሚተዳደር ነው። በተጨማሪም የበሽታ መከላከል እና ደህንነት ፕሮግራም  ፋውንዴሽን በተባለ  ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት  ውስጥ  በአስተባባሪነት ያገለግላል።

የቡድኑ አምበል ማሪዮ ኢልቺ በአንድ የኮካ ኮላ ማከፋፈያ ውስጥ የሽያጭ ሰራተኛ ነው። ለአለም ክለቦች ዋንጫ ወደ አሜሪካ ለመጓዝ አለቃውን ደጋግሞ ማስፈቀዱን እና  የዚህ አመቱን ሙሉ የአመት ፍቃዱን መጠየቁን የሚናገረው ኢልቺ በዚህ አመት ኪዚህ በኋላ ወደየትም መጓዝ እንደማይችል ተናግሯል።

ከአሰልጣኞቹ ጀምሮ 95 በመቶ የሚሆኑት የቡድኑ አባላት ቋሚ ስራቸው እግር ኳስ ብቻ እንዳልሆነ የሚናገረው አምበሉ  ጸጉር አስተካካይ፣ መምህር፣ የሪል ስቴት ወኪል፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና ሌሎችም እንደሚገኙበት አብራርቷል።

ማሪዮ ኢልቺ ብዙ ሰው ይሄ ቡድን እንዴት እዚህ ደረጃ ደረሰ ብሎ ይጠይቅ ይሆናል፣ እኛ እዚህ የተገኝነው ለእግር ኳስ ባለን ፍቅር ብቻ ነው ሲል ተደምጧል።

የኦክላንድ ሲቲ ሙሉ ቡድን ዋጋ 1.23 ሚሊየን ፓውንድ የሚገመት ሲሆን 10 ለ 0 ያሸነፈው ባየር ሙኒክ ደግሞ 770 ሚሊየን ፓውንድ ነው። ይሄ ማለት የጀርመኑ ሻምፒዮን በ700 ዕጥፍ ኦክላንድ ሲቲን ይበልጣል እንደማለት ነው።

በሌላ በኩል የሀሪ ኬን ብቻ አመታዊ ገቢ 18 የኦክላንድ ሲቲን ቡድንን የመግዛት አቅም አለው እንደማለት ነው።

በአስቸጋሪ ፈተና ውስጥ ያለው የኒውዝላንድ ቡድን በአለም ክለቦች ዋንጫ ታሪክ 10 ግብ የተቆጠረበት የመጀመርያው ቡድንም ሆኗል።

በአንተነህ ሲሳይ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top