የንስሓ ልጆቻቸው የሚማሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በተግባር እንዲኖሩ የሚያደርጉት አባት

7 Hrs Ago 176
የንስሓ ልጆቻቸው የሚማሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በተግባር እንዲኖሩ የሚያደርጉት አባት

ላእከ ወንጌል ቀሲስ በእደ ማርያም ይትባረክ ይባላሉ፤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ትምህርት ሥርጭት ኃላፊ ናቸው።

እኚህ አባት የንስሓ ልጆቻቸው በተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራ ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ የሚማሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በተግባር እንዲኖሩ እየሠሩ ይገኛሉ።

482 የንስሓ ልጆቻቸውን በማስተባበር ሃይማኖቱ በሚያስተምረው መሠረት አቅመ ደካሞችን ይረዳሉ፤ ወላጅ የሌላቸው ልጆች ዓለማዊውንም፣ የሃይማኖት ትምህርቱንም እንዲማሩ ያግዛሉ።

በ2017 ዓ.ም ካከናወኗቸው የበጎ ተግባራት ሥራዎች መካከልም እማማ ዘውዲቱ መሸሻ ከሚያሳድጓቸው ልጆች መካከል ለ12ቱ የትምህርት እና የምግብ ወጪ እንዲሸፈን ማገዛቸው፤ ለ12 ችግረኞች ደግሞ ዓመቱን ሙሉ የቤት ኪራይ እንዲከፈል ማድረጋቸው ይጠቀሳል።

ባሳለፍነው እሑድ (ሰኔ 8 ቀን 2017 ዓ.ም) ደግሞ የንስሓ ልጆቻቸው ጉባኤ የተጀመረበትን 11ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በመቄዶንያ የአረጋውያን እና አዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ተገኝተው 316 ሺህ 979 ብር የሚገመት የዓይነት ድጋፍ አድርገዋል።

ድጋፉ የተለያዩ አልባሳትን፣ ዘይት፣ ዱቄት፣ ፓስታ፣ ማካሮኒ እና ሌሎች የምግብ ዓይነቶችን እንዲሁም ሳሙና፣ ፈሳሽ ሳሙና እና የሴቶች የንፅህና መጠበቂዎችን ያካተተ ሲሆን ሁሉም እንደየአቅሙ የሚችለውን ይዞ በማዕከሉ በመገኘት አስረክቧል።

በተጨማሪም እንጂነር ኤፍሬም ጥሩነህ የተባሉ የንስሓ ልጃቸው 288 ሺህ ብር የሚገመት ከጃፓን የመጣ የልብ መመርመሪያ መሣሪያ (ኢሲጂ) ለመቄዶንያ ማስረከባቸው በመርሐ-ግብሩ ላይ ተገልጿል።

ላእከ ወንጌል ቀሲስ በእደ ማርያም ይትባረክ ከዚህ በፊትም ለመቄዶንያ የሕንፃ ማጠናቀቂያ ገቢ ማሰባሰቢያ ላይም ከእነዚሁ የንስሓ ልጆች ያሰባሰቡትን 230 ሺህ ብር ገቢ አድርገዋል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙት የቡኖ በደሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም፣ “ሁላችንም እንደ ቀሲስ በእደ ማርያም የየራሳችንን ሚና ብንወጣ ኖሮ ቢንያም ብቻውን አይለፋም ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።

ላእከ ወንጌል ቀሲስ በእደ ማርያም ይትባረክ እየሠሩት ያለው በጎ ተግባር የሚመሰገን መሆኑን ገልጸው፣ “ሁሉም የሃይማኖት አባት ከዚህ መልካም ሥራ ሊማር ይገባል” ብለዋል።

“ቢንያም በለጠ (የክብር ዶክተር) እንደ ሻማ እየቀለጠ ለሌሎች እየሠራ ነው፤ እኛም እንደየአቅማችን ማገዝ አለብን” ሲሉም አክለዋል።

መቄዶንያ ሲቋቋም “ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው” በሚል መርሕ በመሆኑ የሁሉም ሃይማኖቶች አባቶች በዚሁ መርሕ መሠረት ምዕመኑን አስተባብረው ድጋፋቸውን እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

ላእከ ወንጌል ቀሲስ በእደ ማርያም ይትባረክ በመርሐ-ግብሩ ላይ ለንስሓ ልጆቻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ “ቢንያም (የክብር ዶክተር) ራሱን ለሌሎች የሰጠ፣ በበጎ ተግባር ሥራው ለሁሉም ሰው ምሳሌ የሚሆን ነው” ብለዋል።

“እናንተም ‘ብራብ አብልታችሁኛልና፤ ብጠማ አጠጥታችሁኛልና፤ ብታረዝ አልብሳችሁኛልና’ የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል ስለተገበራችሁ ልትመሰገኑ ይገባል” ሲሉ የንስሓ ልጆቻቸውን አመስግነዋል።

የመቄዶንያ መሥራች የክብር ዶክተር ቢንያም በለጠ በበኩሉ፣ ላእከ ወንጌል ቀሲስ በእደ ማርያም ይትባረክ በዚህ ልክ አስበው ላደረጉት ድጋፍ አመስግኗል።

ማዕከሉ የሁሉም ኢትዮጵያዊ በመሆኑ የሁሉም እምነት አባቶች በዚሁ መልክ ምዕመኑን አስተባብረው ድጋፍ የማድረግ ልምዱን እንዲያዳብሩም ጥሪ አቅርቧል።

በዮናስ በድሉ

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top