በአማራ ክልል የቀበሌ መሪዎች ስልጠና በመሰጠት ላይ ነው። ስልጠናው በባሕር ዳር ከተማም እየተሰጠ ይገኛል።
"ቀበሌዎቻችንን በማጽናት ሁለንተናዊ እምርታ እናስመዘግባለን" በሚል መሪ መልዕክት ስልጠናው ለከተማ እና ለገጠር የቀበሌ መሪዎች ነው እየተሰጠ የሚገኘው።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ባስተላለፉት መልእክት በአማራ ክልል በአሁኑ ወቅት ከ4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል፤ በመኾኑም የቀበሌ መሪዎች ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ በርብርብ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
መንግሥት ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል ያሉት አቶ አረጋ ለግብርና ግብዓት ከፍተኛ ገንዘብ ድጎማ መደረጉን ጠቅሰዋል። ስለሆነም በድጎማ የተገዛው ግብዓት ወደ ተፈለገው ሥፍራ ተጓጉዞ ለተፈለገው ዓላማ ይውል ዘንድ ከመሪዎች ብዙ ይጠበቃል ነው ያሉት።
ሕዝብን እያማረረ ያለው የኑሮ ውድነትን ችግር ለመቅረፍ ገበያውን በሥርዓት መመራት ይገባዋል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ፤ ነዳጅ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለውና እጥረቱ እንዲከሰት እያደረጉ ያሉትን ሕገ ወጦችን አደብ ማስገዛት በዋናነት የመሪዎች የሥራ ድርሻ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ብልጽግና በብዙ መሰዋዕትነት የተወለደ ትልቅ ፓርቲ መሆኑን አስታውሰው፤ ለውጡ ከውስጥም ከውጭም በብልሃት እና በቅንጅት ስለተመራ ባለፉት ስድስት ዓመታት በርካታ ስኬቶችን አምጥቷል ብለዋል።
ብልጽግና በተለየ መልኩ የቀበሌ መሪዎች በግምገማ እና ስልጠና ማለፍ አለባቸው ብሎ እንደሚያምን ያነሱት አቶ ይርጋ፤ የቀበሌ መሪዎች ሥልጠና በክልሉ በሁሉም ዞኖች፣ ከተማ አሥተዳደሮች እና ቀበሌዎች ተጀምሯል፤ ለተከታታይ ቀናትም ይቆያል ብለዋል።
ከመጀመሪያ ዙር ሥልጠና ግብዓት በመውሰድ ሁለተኛው ዙርም ስልጠና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ይርጋ ተናግረዋል።
በቀበሌ መሪዎች ላይ ያለው የመሪነት ክፍተት ካልተስተካከለ በክልሉ ያለውን የሕግ ማስከበር ሥራ በፍጥነት መቋጨት አይቻልም ነው ያሉት ኀላፊው።
በቀጣይ ሦስት ወራት በክልሉ ያልተቋጨውን ሕግ የማስከበር ሥራ ለማጠናቀቅ መንግሥት ዝግጅት አድርጓል ያሉት አቶ ይርጋ ለዚህ ትልቁ አቅም ቀበሌ ላይ ያለው መዋቅር መሆኑን ጠቅሰዋል። ሕዝቡ ተደራጅቶ መሪዎችን እና ልማቱን እየደገፈ መሆኑንም አቶ ይርጋ ጠቁመዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው የባሕር ዳር ከተማን ልማት ለማፋጠን እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እውነተኛ መሪዎች መኾን ይጠበቅብናል ብለዋል።
ሰላማችንን በበለጠ በማጽናት፤ ልማትን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ያሉት አቶ ጎሹ ባሕር ዳርን በዓለም የቱሪዝም መዳረሻ ውብ፣ ማራኪ፣ ምቹ ለማድረግ መትጋት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ከቀበሌ መሪዎች ከፍተኛ ሥራ ይጠበቃል ማለታቸውን ከእማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።