የታላቁ አንዋር መስጅድን ስም እና ታሪክ የሚመጥን የበጎነት ሥራ የሚሠሩ ወጣቶች

12 Hrs Ago 1149
የታላቁ አንዋር መስጅድን ስም እና ታሪክ የሚመጥን የበጎነት ሥራ የሚሠሩ ወጣቶች

የረመዳን ወር በጎ ሥራዎች የሚንፀባረቁበት፣ ሁሉም ሰው ያለውን በማካፈል አብሮነትን በሚያጠናክሩ ሁነቶች በጾም እና በጸሎት የሚበረቱበት ወር ነው።

በአንዋር መስጅድ በየዓመቱ የሚዘጋጀውን የኢፍጣር መርሐ-ግብር ምን ድባብ አለው? ምን ምን ተግባሮችስ እንደሚከናወኑ ኢቢሲ ዶትስትሪም ቅኝት አድርጓል። 

ይህ አይነቱ በጎነት ላለፉት አምስት ዓመታት ሳይቋረጥ እየተዘጋጀ መቀጠሉን በአንዋር መስጅድ የበጎ ተግባር ተሳታፊ ወጣቶች ኅብረት አስተባባሪ ሐይደር ዳውድ ነግሮናል።

የወጣቶች ኅብረቱ ከ200 በላይ አስተናጋጆችን በውስጡ ያቀፈ ሲሆን መርሐ-ግብሩ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ምግብ ከማሰናዳት ጀምሮ በኢፍጣሩ ላይ የሚገኙ ሰዎችን መመገብ፣ ዕቃዎችን ማጠብ እና መስጅዱን ማፅዳት ሥራዎችን በትብብር ይሠራሉ። 

በኢፍጣር መርሐ-ግብሩ በቀን ከ200 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ከ1 ሺህ 500 በላይ ሰዎች እንደሚሳተፉ ወጣት ሐይደር ገልጿል።

በኢፍጣር መርሐ-ግብሩ ላይ የሚሳተፉት ጧሪ የሌላቸው አቅመ ደካሞች፣ አካል ጉዳተኞች እና ሌሎች ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች መሆናቸውን የገለጸው አስተባባሪው፣ ሥራው የተጀመረው በኮሮና ወቅት እንደነበር አስታውሷል። 

የኢፍጣር መርሐ-ግብሩ በአንዋር መስጅድ ወሩን ሙሉ ያለምንም ማቋረጥ የሚከናወን እንደሆነም ገልጿል። 

ታላቁ አንዋር መስጅድ እንደ ግዝፈቱ እና ቀደምት ታሪካዊ ከሚባሉ መስጅዶች አንዱ እንደመሆኑ ታላላቅ የሃይማኖት አባቶች እና ኡላማዎችን በውስጡ ያቀፈ እና ስሙን የሚመጥን ሥራ ለመሥራት እየተሞከረ እንደሚገኝም ገልጿል። 

አቅመ ደካሞች በየአካባቢው ይገኛሉ የሚለው ወጣቱ፣ በየአካባቢው የሚገኙ ወጣቶች በመተባበር ይህን በጎ ተግባር ምሳሌ በማድረግ ወገኖቻቸውን በመርዳት  ለነገ ቤታቸው ጽድቅን የሚያስገኝ ሥራ ላይ ለመሳተፍ መሽቀዳደም አለባቸው ሲልም መክሯል።

በኔፍታሌም እንግዳወርቅ

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top