38ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ የኅብረቱን አዲስ ኮሚሽነር በመምረጥ እና በአህጉሪቱ መጻኢ ዕጣ ፋንታ ላይ በመምከር መጠናቀቁ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ከቻይናው ሚዲያ ሲጂቲኤን ጋር በመተባበር በ38ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ በተነሱ ዋና ዋና ጉዳዮች እና ተመራጩ ኮሚሽነር በሚጠብቋቸው ኃላፊነቶች ዙሪያ ከምሁራን ጋር ውይይት አድርጓል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት ዶ/ር ዮናስ አሽኔ ፤ የአፍሪካ ኅብረት በአህጉሪቱ ያለውን የፖለቲካ ምህዳር በማጠናከር እና እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችን በመፍታት ላይ ይበልጥ ውጤታማ ሥራዎችን ሊሰራ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
አዲሱ የኅብረቱ ኮሚሽነር ኢኮኖሚያዊ ውህደትን እና ንግድን በማጠናከር ለልማት እና መረጋጋት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮችን ማጉላት እንደሚጠብቅባቸውም አንስተዋል፡፡
ተመራጩ ኮሚሽነር የአፍሪካን ውስብስብ ችግሮች በብቃት ለመፍታት የሚያስችል ሰፊ የዲፕሎማሲ ልምድን ይዘው ይመጣሉ ብዬ እጠብቃለሁ ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላም እና ደህንነት ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ዮናስ አዳዬ ናቸው።
የአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና የፀጥታ መዋቅር ከክልላዊ ድርጅቶች ጋር በመሆን የግጭት አፈታት ላይ ተጽዕኖ ማሳደር አለመቻሉንም ምሑሩ አንስተዋል። እነዚህ ድክመቶች ኅብረቱ ለውጭ ጣልቃገብነቶች ውጤታማ ምላሽ እንዳይሰጥ እንቅፋት ሆነዋል ብለዋል።
በአፍሪካ እየተከሰቱ ያሉት ግጭቶች ምርታማነትን በመቀነስ የአቅርቦት ሰንሰለቶችን እያስተጓጎሉ ይገኛሉ ያሉት ዶ/ር ዮናስ አዳዬ፤ የሰላም እና የጸጥታ እጦት በአህጉሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ልማት ላይ ከፍተኛ እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑን አንስተዋል።
የምጣኔ ሐብት ባለሙያው ዶ/ር ቴዎድሮስ መኮንን በበኩላቸው የተዋሃደች አፍሪካ በንግድ ውድድር እና የአየር ንብረት ለውጥ ውስጥ ያሉ ችግሮችን በተሻለ መንገድ መፍታት ትችላለች ብለዋል።
አሕጉሪቱ የተቀናጀ ግንባር መፍጠር ከቻለች ዓለም አቀፋዊ ተጽኖዋን ማሳደግ ትችላለች ሲሉም ገልጸዋል።
በአፍሪካ ሰዎች እና ሐሳቦች ያለገደብ መንቀሳቀስ አለባቸው ያሉት ባለሙያው ፤ ይህም ለአፍሪካ ዕድገት ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በፍጥነት እየተለዋወጠ ከሚገኘው የዓለም ጂኦ ፖለቲካ እና የምጣኔ ሐብት ዕድገት ጋር እኩል ለመራመድ አፍሪካ ሀብቶቿን እና ክህሎቶችን አዋህዳ መጠቀም እንዳለባትም ዶ/ር ቴዎድሮስ ምክረ ሀሳባቸውን አቅርበዋል፡፡
ሰለሞን ከበደ