ስሟን በዓለም አቀፍ የሥነ-ጥበብ ከፍታ ላይ የጻፈችውን ጁሊ ምህረቱ

12 Hrs Ago 367
ስሟን በዓለም አቀፍ የሥነ-ጥበብ ከፍታ ላይ የጻፈችውን ጁሊ ምህረቱ

ጁሊ ምህረቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በረቂቅ እና ዘመናዊ ሥዕሎቿ የምትታወቅ ኢትዮ-አሜሪካዊት አርቲስት ነች።

ሥራዎቿ በታሪክ፣ በሥልጣኔ፣ በከተሜነት፣ በማኅበራዊ ማንነት እና በዘመናዊው ዓለም ፈጣን ለውጥ ላይ ያተኮሩ እና ቀጣይነት ያለው ቅኝት ላይ ያተኮሩ ናቸው።

የተወለደችው እ.አ.አ በ1970 በአዲስ አበባ ነው፡፡ አባቷ የኢትዮጵያ የጂኦግራፊ ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ እናቷ ደግሞ አሜሪካዊት መምህርት ናቸው።

ጁሊ የሀገር ውስጥ ፖለቲካ ውጥንቅጡ ሲበዛ እ.ኤ.አ በ1977 ከቤተሰቦቿ ጋር ወደ አሜሪካዋ ሚችጋን በማቅናት በምሥራቅ ላንሲንግ አካባቢ መኖር ስትጀምር ሰባት ዓመቷ ነበር።

በ1992 ሚችጋን ከሚገኘው ካላማሱ ኮሌጅ፣ በሥነ ጥበብ የመጀመሪያ ዲግሪዋን አግኝታለች፡፡ በ1997 ከሮድ አይላንድ ዲዛይን ትምህርት ቤት (RISD) በ‘ፋይን አርት’ እና ሕትመት ሥራ ሁለተኛ ዲግሪዋን አግኝታለች።

ጁሊ በውስብስብ፣ መልከ ብዙ እና ረቂቅ ሥዕሎቿ ትታወቃለች። ብዙውን ጊዜ ሥራዎቿን የምትጀምረው በሥነ ሕንፃ፣ በከተማ ዕቅድ እዲሁም በከተማ ውበት ነው። ሥዕሎቿ ረቂቅ እና ብዙ መመራመር የሚጠይቁ የአንድን ቦታ "psychogeography" የሚፈጥሩ ናቸው።

በሥዕሎቿ ውስብስብ፣ ጠንካራ እና አመራማሪ የሆኑ እይታን ትፈጥራለች። የእጅ ጽሑፍ አጣጣልን እና የተለያዩ ቀለማትን ተጠቅማ በምትሠራቸው ሥዕሎቿ የሰው ልጆችን ማኅበራዊ እንቅስቃሴ፣ የአየር ንብረት ሁኔታን እንዲሁም ሌሎች ከሰው ልጆች ሕይወት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ትገልጻለች፡፡

ከተሜነት እና ዓለም አቀፍ ከተሞች፣ ታሪክ እና የሥልጣን መዋቅሮች፣ ስደት፣ መፈናቀል እና ማንነት እንዲሁም ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እይታዎች በሥዕሎቿ የምታተኩርባቸው ናቸው፡፡

በግሏም ከ10 በላይ የሥዕል ዐውደ ርዕዮችን አዘጋጅታ ለአድናቂዎቿ አቅርባለች፡፡ ሥራዎቿ እንደ ‘ዊትኒ ቢየንያል፣ ቬኒስ ቢያንናል፣ ኢስታንቡል ቢየንያል፣ ካርኔጌ ኢንተርናሽናል እና ዶክመንታ’ ባሉት ታላላቅ ዓለም አቀፍ ዝግጅቶች ውስጥ ተካትተውላታል።

ጁሊ ምህረቱ በርካታ ታላላቅ ሽልማቶችን እና ክብሮችን በማግኘት በዘመኑ ታላላቅ የኪነ-ጥበብ ሰዎች ተርታ ስሟን አስፍራለች።

ካገኘቻቸው ሽልማቶች መካከልም በ2005 ‘ማካርተር ፌሎውሺፕ (Genius Grant)’ ፣ በ2005 አሜሪካን ሥነ-ጥበብ አዋርድ፣ በ2007 ‘በርሊን አዋርድ’፣ በ2015 የአሜሪካ የሀገር ውስጥ የሥነ-ጥበብ ዘርፍ የሜዳልያ ሽልማት እንዲሁም በዚህ የፈንጆች ዓመት "Officer of the Ordre des Arts et des Lettres" ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ጁሊ የአሜሪካ የሥነ ጥበብ ባለሙያዎች ማኅበር እንዲሁም የአሜሪካ የሥነ ጥበብ እና የሳይንስ አካዳሚ አባል ነች።

ከሥነ-ጥበብ ባሻገርም ማኅበራዊ ፍትህ እና የባህል ጥበቃ ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ ታደርጋለች። በአሁኑ ወቅት የምትኖረው እና ሥራዎቿን የምታቀርበው በዋናነት በኒው ዮርክ ከተማ እና በጀርመኗ በርሊን ከተማ ነው።

በረቂቅ የሥዕል ሥራዎቿ አድማስን የተሻገሩ የሰው ልጅ ሥልጣኔዎችን እና ውስብስበ ማኅበራዊ መስተጋብርን ማሳየቷን ቀጥላለች።

ጁሊ ምህረቱ ኢትዮጵያ ለማንነቷ መሰረት መሆኗን አልዘነጋችም። ሥራዎቿ የኢትዮጵያን አሻራ የሚያሳዩ መሆናቸው የሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የመስታወት ቅብ የመሰሉ ሥዕሎቿ ማሳያ መሆናቸውን ዘ አርትስ ስቶሪ ላይ ተጠቅሷል።

በ2016 በአዲስ አበባ "The Addis Show" በሚል ርዕስ "Homecoming show" የተሰኘ የሥዕል ዐውደ ርዕይ እንዳቀረበች መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

እ.ኤ.አ መጋቢት 2023 "ከፍታ" በተባለው እና የኢትዮጵያን ወጣቶች ተጠቃሚ ባደረገው የሥዕል ጨረታዋ በ"Amref Health Africa የክብር ዕውቅና ተሰጥቷታል።

"Amref Health Africa" የምታደርገው ተሳትፎዋ በተለይ ፍትሃዊ የጤና አገልግሎትን ለማስፈን እንዲሁም "የአፍሪካ ባህል ለአፍሪካውያን" ብላ በምትገልጸው እንቅስቃሴ ላይ የራሷን አሻራ በማኖሯ ደስተኛ መሆኗን ትገልጻለች፡፡

ይህም የወጣት ኢትዮጵያውያንን ሕይወት እና የወደፊት ዕድገት ለማሻሻል በሚሠሩ ሥራዎች ላይ ለመሳተፍ ያላትን ፍላጎት ያመለክታል።

በለሚ ታደሰ

#etv #EBC #ebcdotstream #JulieMehretu #ArtCar20  


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top