በጃፓን ከመዋዕለ- ህጻናት ጀምሮ ባሉ ትምህርት ቤቶች ከመማሪያ ክፍሎች ጀምሮ አካባቢን የማፅዳት ባህል እንደ አንድ የትምህርት አይነት በስርዓተ ትምህርት ውስጥ የተካተተ ነው።
ጃፓናውያን ከህጻንነታቸው ጀምሮ በኦ-ሶንጆ ስርዓት ተቀርፀው ያድጋሉ። ኦ-ሶጂ ይባላል። ይህ ከጥንት ጀምሮ ሲተላለፍ የመጣ ሀይማኖታዊ መሰረት ያለው የፅዳት ባህል የጃፓናውያን የፅዳት ምስጢር ሆኗል።
በዚህ የስርዓተ ትምህርቱ አንድ ክፍል በሆነው ኦ -ሶጂ መሰረት ከመዋዕለ ህጻናት ጀምሮ ባሉ የጃፓን ትምህርት ቤቶች የቀኑ ትምህርት ሊጠናቀቅ ሲቃረብ ተማሪዎች ከ15 እስከ 20 ደቂቃ የሚወስደውን የቀኑን የፅዳት ፕሮግራም ለማከናወን ይዘጋጃሉ።
ለዚሁ ተብሎ የተዘጋጀ የኦ-ሶጂ መዝሙር (ተማሪዎች በፅዳት ወቅት የሚሰሙት) ሙዚቃ ይከፈታል። ወዲያውም በቡድን በቡድን የተከፋፈሉት ተማሪዎች መጥረጊያና መወልወያቸውን ይዘው እንዲያፀዱ የተወሰነላቸውን ቦታ መጥረግና መወልወል ይጀምራሉ።

በዚህ ወቅት የፅዳት ሰራተኞች ሊያግዟቸው አይሞክሩም። ይህ ጊዜ ተማሪዎች ከክፍላቸው ጀምሮ የሚያፀዱበት ጊዜ ስለሆነ የፅዳት ሰራተኞቹ ተማሪዎቹን ከመከታተል ውጭ ማፅዳት ወይም ማገዝ አይችሉም።
እነዚህ ጥቂት የፅዳት ባለሞያዎች ከሶስተኛ ክፍል በታች ለሆኑ ተማሪዎች መፀዳጃ ክፍሎችን በማፅዳት ያግዛሉ። ከዛ ውጭ የእነሱ ስራ ቆመው ማየት ብቻ ነው።
ከአራተኛ ክፍል ጀምሮ ያሉ ተማሪዎች ጋር ደግሞ መፀዳጃ ቤቶችንም የማፅዳት ሀላፊነት አለባቸው። ለጃፓኖች ኦ-ሶጂ የፅዳት ምስጢር ብቻ አይደለም የመታዘዝ እና በጋራ የመስራትን ልምድ እንዲያዳብሩ የሚያደርግ ባህል ነው።
በዚህ አይነት ጥንታዊ ባህል ውስጥ ያለፉ ጃፓናውያን በስራ ቦታም በመኖሪያ ቤት እንዲሁም በመንገድ ላይ ንፅህና እንደ ባህል አብሯቸው የሚኖር ነው። ከዚህም አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባሉ ስፖርታዊ ክንውኖች ላይም ጃፓኖች በተደጋጋሚ ጊዜያት ስታዲየሞችን አፅድተው ሲወጡ ተስተውሏል።

በቶኪዮና የመሳሰሉ የጃፓን ከተሞች በየመንገድ ዳር የተቀመጠ ብዙ የቆሻሻ መጣያዎችም አይገኙም። በእነዚህ ከተሞች ጥቂት የሚባል የቆሻሻ መጣያ ቢኖርም ቱሪስቶችና በዚህ ባህል ያላለፉ ካልሆኑ በአብዛኛው ጃፓናውያን ቆሻሻቸውን በመንገድ ላይ ባሉ የቆሻሻ ማስቀመጫዎች ውስጥ ከመጣል ይልቅ ተሸክመው ወደቤታቸው በመሄድ ይታወቃሉ።
ለዚህም ነው ጃፓን ብዙ የቆሻሻ መጣያ የሌለባት ግን ንፁህ ከተማ በመሆን የምትታወቀው። በዚህች ሀገር በተለይ በቶኪዮ የጎዳና ላይ የቆሻሻ ማስቀመጫዎች ለአንድ ሺህ ህዝብ አንድ የቆሻሻ ማስቀመጫ ብቻ ነው ያለው።

በአንዳንድ ቱሪስቶች በሚበዙባቸው አካባቢዎች ደግሞ በፀሀይ ሀይል የሚሰሩ የቆሻሻ ማስቀመጫዎች ተቀምጠዋል። እነዚህ በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ የሚሰሩ የቆሻሻ መጣያዎች ሲሞሉ የፅዳት አገልግሎት ወደሚሰጠው ድርጅት ምልክት የሚሰጡ ናቸው። የፅዳት አገልግሎት ሰጭዎቹ ይህ ምልክት እንደደረሳቸው በተላከላቸው አድራሻ መሰረት ወደ ሞላው የቆሻሻ ማስቀመጫ ያለበት ቦታ በመሄድ ቆሻሻውን ገልብጠው ለአገልግሎት ዝግጁ እንዲሆን ያደርጉታል።
ሁሉም ጃፓናዊ በሚባል መልኩ ንፅህናን አካባቢን ማፅዳት ባህል አድርገው ስለሚያድጉ ጃፓን ከተሞቿ ሁሌም ንፁህ ናቸው። የባቡር ጣቢያዎች መአዛ ያውዳል። ጎዳናዎቿ ላይ አንድም ቆሻሻ አይታይም።
ይህ የጃፓን የንፅህና ምስጢር የሆነውን የ ኦ-ሶጂ መልካም ተሞክሮ ከራሳቸው ባህልና የስርዓተ ትምህርት ጋር በማዋሀድ በጀርመን፣ሲንጋፖር፣ ህንድ፣ ደቡብ ኮሪያና ፣ ኢንዶኔዥያ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ለመተግበር እየሞከሩ ይገኛሉ።
በዋሲሁን ተስፋዬ