የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የብሔራዊ ባንክ መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሪ ክምችትን በ235 በመቶ ማሳደጉን የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ገልጸዋል።
በማሻሻያው ቁልፍ ትግበራዎች አንዱ በሆነው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያ በ50 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያው እንዲወሰን መደረጉን ተናግረዋል።
በዚህም ማሻሻያ ከዚህ ቀደም የነበረው ንግድ ባንኮች እና በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሪ ለብሔራዊ ባንክ እንዲያስተላልፉ የሚያስገድደው አሰራር እንዲቀር ተደርጓል።
የውጭ ምንዛሪ አገልግሎት የሚሰጡ ቢሮዎች ወደ ስራ እንዲገቡ በመደረጉም የውጭ ሀገር ገንዘቦችን መሸጥ እና መግዛት ቀላል እንዲሆን ማስቻሉንም ነው አቶ ማሞ ምህረቱ ገለጹት።
ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የንግድ ድርጅቶች ከውጭ ሀገራት በውጭ ምንዛሪ መበደር የሚችሉበት አሰራር መዘርጋቱንም አስታውቀዋል።
በአጠቃላይ በውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ላይ ሥር ነቀል የሚባል ለውጥ ማምጣት ተችሏል ነው ያሉት።
ይህ ማሻሻያ በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን የውጭ ምንዛሪ ፍሰት በማሳደግ የውጭ ምንዛሪ የሚፈልጉ ቢዝነሶች በቀላሉ የሚያገኙበት እድል ፈጥሯልም ብለዋል።
በመደበኛው እና በትይዩ ወይም ጥቁር ገበያ መካከል ያለው የውጭ ምንዛሪ ተመን አሁን ላይ በከፍተኛ መጠን መጥበቡን ገልፀዋል።
ከማሻሻያው በኋላ በዚህ ዓመት የሸቀጦች ወጪ ንግድ ገቢ በ119 በመቶ፣ የአገልግሎት ወጪ ንግድ ገቢ በ23 በመቶ ከውጭ ሀገር በሀዋላ የሚላክ ገንዘብ በ22 በመቶ እንዲሁም የውጭ እርዳታ በ93 በመቶ ማደጉንም ተናግረዋል።
የብሔራዊ ባንክ መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ በፊት ከነበረው በ235 በመቶ ማደጉንም የባንኩ ገዥ ማሞ ምህረቱ አስታውቀዋል።