ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባለፉት ሳምንታት ከመላው ኢትዮጵያ ከተውጣጡ ከንግዱ ማኅበረሰብ፣ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ ከመምህራን ተወካዮች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን ተወካዮች ጋር ሁሉን አቀፍ እና ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል።
ውይይቶቹ በየዘርፉ ያሉ ፍላጎቶችንና ተግዳሮቶችን ለክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ፊት ለፊት ለማቅረብ እድል የፈጠሩ፣ ከዚህም አኳያ በአጭር ጊዜ ሊፈቱ የሚችሉ ጉዳዮች አቅጣጫ የተሰጠባቸው እና በረጅም ጊዜ የሚፈቱት ላይ ደግሞ ትልም የተቀመጠባቸው ሆነው በስኬት ተጠናቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ቆይታ የማኅበረ-ኢኮኖሚ ግንባታን የሚያፋጥኑ፣ ተወዳዳሪነትን እና ምርታማነትን የሚጨምሩ እንዲሁም የሥራ ባህልን የሚያሳድጉ ተግባራትን ይበልጥ እንዲያጎለብቱና የሥራ እድል ፈጠራን እንዲያስፋፉ አበረታትተዋል።
የሃገራዊ ልማት ውጥኖችን በማሳካት ረገድ የንግዱ ማኅበረሰብ ያለው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ መንግሥት ለዘርፉ ምቹ የሆነ ሕጋዊና ነባራዊ ሁኔታ እንዲፈጠር የማስቻል ሚናውን በከፍተኛ ትኩረት ይሰራል።
ከፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጋር በተደረገው ውይይት ቀጣይነት ላለው የሰላምና ደህንነት፣ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና ጠንካራ ሀገራዊ አንድነት ሁሉን አቀፍ አስተዳደር ያለውን አስፈላጊነትን በማንሳት የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ገንቢ ተሳትፎና የሰከነ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
መንግሥት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚያደርገው ቀጣይነት ያለው ምክክር የሚመነጨው ሃሳብ ያለው ሁሉ በሃገረ መንግሥት፣ በማህበረ ኢኮኖሚና ዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ንቁ ተዋናይ እንዲሆኑ የጀመረውን አካታች የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አጠናክሮ ለማስቀጠል ካለው ጽኑ እምነት ነው።
ከመምህራን እና የጤና ባለሙያዎች ጋር ባደረጓቸው ምክክሮች ባለሞያዎቹ በሃገር እና ትውልድ ግንባታ ሂደት ላበረከቱት ወሳኝ ሚና አመስግነው፣ በዘርፎቹ የሚታዩ ችግሮችን ለማሻሻል መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
ሃገራዊ ትልሞች የሚሳኩት የሰብዓዊ አቅም ልማት ስራዎች በተሳካ ሁኔታ ሲከናወኑና የዜጎች ሁለንተናዊ ጤንነት ሲጠበቅ በመሆኑ ዘርፎቹ ለሃገር ግንባታ ቁልፍ ሚናቸውን በበለጠ ሁኔታ እንዲወጡ በዘርፎቹ ያሉ ተግዳሮቶችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት መንግሥት ቁርጠኛ ነው።
የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ጋር ባደረጉት ውይይት የኢትዮጵያን ባህላዊ ማንነትና እሴት በመቅረጽ እና ማህበራዊ ትስስርን በማጎልበት እያደረጉ ያሉትን ጥረቶችን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
ኪነ-ጥበብ ለሃገረ-መንግሥት ግንባታና ለመልካም ማኅበራዊ እሴቶች እነጻ የማይተካ ሚና ያለው በመሆኑ ኪናዊ ፈጠራን የሚያበረታታ ምኅዳር እንዲጎለብት መንግሥት ተገቢውን ሃላፊነት ይወጣል።
ከግል እና የሕዝብ መገናኛ ብዙኀን እና የሕዝብ ግንኙነት ተወካዮች ጋር በነበራቸው ምክክርም ነፃ እና ኃላፊነት የሚሰማው ሚዲያ ዲሞክራሲን ለማስፈን ያለውን ወሳኝ ሚና አፅንዖት ሰጥተው፣ በዚህ ረገድ መንግሥት የሚጠበቅበትን ሚና እንደሚወጣ ቃል ገብተዋል።
ኢትዮጵያዊ እሴትን የተላበሱ፣ ብሔራዊ ጥቅምን እንደ መልህቅ የያዙና በሙያዊ ሥነ-ምግባር የታነጹ ሚዲያዎች እንዲበዙና ለሃገረ-መንግሥት ግንባታ ምሰሶ ሆነው እንዲቆሙ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ያረጋግጣል።
በአጠቃላይ መንግሥት ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ያደረጋቸው ውይይቶች የሚነሱ ጉዳዮችን በማድመጥ ለዘላቂ ሰላም፣ ዲሞክራሲና ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ልማት እንዲሁም ማኅበረሰባዊ ተጠቃሚነት እንቅፋት የሆኑ ችግሮችና ሥጋቶችን ለመለየት መልካም እድል የፈጠሩ ነበሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም መንግሥት ለሃገር ሁለንተናዊ ብልጽግና ያለውን ቁርጠኝነት በመግለጽ፣ ከሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች የተነሱ ጉዳዮች ወደ እቅድ ተቀይረው ደረጃ በደረጃ እንደሚፈቱ ያረጋገጡበት ነበር።
በውይይትመድረኮቹ መግባባት የተደረሰባቸው ጉዳዮችና የተሰጡ አቅጣጫዎች ተፈጻሚነት እንዲኖራቸው ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ በዚህ አጋጣሚ መንግሥት ያሳስባል።
ሀገራችንን ወደሚፈለገው ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማሻገር ሁሉም የማህብረሰብ ክፍል የየራሱ ድርሻ እንዳለው መንግሥት ያምናል።
ሀገራዊ ራዕያችን የሚሳካውም በሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ጥረትና ትጋት ነው፤ በሃገሪቱ የሚታዩ ተግዳሮቶችም መፍትሄ የሚያገኙት፣ ስኬቶቻችንም የበለጠ የሚጎለምሱትና የኢትዮጵያ በጎ ገጽታ የሚጎላው ቀርቦ በመነጋገር፣ በዓላማ ላይ በመግባባት እንዲሁም የሚያጋጥሙ ችግሮችን እየፈቱ በመሄድ ነው።
ለዚህም መንግሥት ከሕዝብ ጋር የሚያደርገውን ውይይት አጠናክሮ ይቀጥላል።