የ2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መጠናቀቁን ተከትሎ የወረዱት ክለቦች ቅሬታ እያሰሙ ይገኛሉ።
አክሲዮን ማኅበሩ በውድድር አመቱ ተግባራዊ ሊያደርገው አዲስ ያጸደቀው የክለቦች የፋይናንስ አስተዳደር መመሪያ በሚገባ ተግባራዊ አልሆነም ይላሉ ክለቦቹ።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ያወጣውን መመሪያ ጥሰዋል ያላቸው ክለቦች ላይ ክስ መስርቶ ጥፋተኛ የሆኑትን አሳውቆ እንደነበርም ይታወሳል።
ሆኖም አወዳዳሪው አካል ህጉን የተላለፉት ክለቦች ላይ ዕርምጃ ሳይወስድ የውድድር ዘመን ተጠናቋል።
አክሲዮን ማኅበሩ ያወጣውን መመሪያ አክበረን ተወዳድረናል የሚሉት የወረዱት ክለቦች ህጉን ካላከበሩት ጋር እኩል መዳኘት የለብን ነው መከራከሪያቸው።
ጉዳዩን በተመለከተ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ምላሽ ሰጥቷል።
የአክሲዮን ማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ ክፍሌ ሰይፈ ጉዳዩ በሂደት ላይ ያለ መሆኑን እና ገና ውሳኔ እንዳላገኘ ተናግረዋል።
"በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ መሰረት ከ15ኛ እስከ 18ኛ ሆነው ያጠናቀቁ ክለቦች አሁን ባለው ሁኔታ ወራጅ ናቸው" ያሉት ሥራ አስኪያጁ በፍርድ ቤት የተያዘው ጉዳይ ጭምር ከተጠናቀቀ በኋላ ሁሉም ነገር ይፋ እንደሚሆን አሳውቀዋል።
በዚህ አመት እንዲተገበር ሁሉም ክለቦች የተስማሙበት የፋይናንስ አስተዳደር መመሪያን ተግባራዊ ለማድረግ አድካሚ እንደ ነበር የገለጹት ክፍሌ ሰይፈ በፍርድ ሂደት ላይ ያሉ በርካታ ጉዳዮች እንዳሉም ተናግረዋል።