የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በፖፕ ፍራንሲስ ህልፈት ህይወት ሐዘን ውስጥ በገባችበት በዚህ ጊዜ የዓለም ትኩረት ወደ ሲስቲን ቤተ ክርስቲያን ዞሯል፡፡
በዚያም ቀጣዩን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ለመምረጥ የካርዲናሎች ጉባኤ በቅርቡ ስብሰባ የሚያካሂድ ይሆናል።
ታዲያ በምርጫው ላይ እስከ 138 የሚደርሱ እና እድሚያቸው ከ80 ዓመት በታች የሆኑ ካርዲናሎች በምስጢራዊ የምርጫ ስነ-ስርዓት አዲስ ጳጳስ እስኪመረጡ ድረስ ብቻቸውን ይሰበሰባሉ።
ቀጣዩን ጳጳስ ለመሾምም ሁለት ሶስተኛ ድምጽ እንደሚያስፈልግ ይነገራል፡፡
ከእጩዎቹ መካከል ከፊሊፒንስ የመጡት የ67 ዓመቱ ብፁዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግል በምርጫው በግንባር ቀደምትነት ተቀምጠዋል። ከፖፕ ከፍራንሲስ ጋር ባላቸው የቅርብ ግንኙነት የሚታወቁት ሉዊስ አንቶኒዮ ታግል፣ “የእስያ ፍራንሲስ” የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል።
በሌላ በኩል የ70 ዓመቱ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ከጣሊያን የመጡ ጠንካራ ተፎካካሪ ናቸው። እ.አ.አ ከ2013 ጀምሮ የቫቲካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉት ካርዲናል ፒዬትሮ፤ በዲፕሎማሲያዊ ልምዳቸውም ይታወቃሉ።
የ72 ዓመቱ የሃንጋሪ ብፁዕ ካርዲናል እና የቀኖና ህግ ምሁር የሆኑት ፒተር ኤርድዶ ሌላው ተፎካካሪ ናቸው።
ሌላኛው በምርጫ ውስጥ የተካተቱት የ76 ዓመቱ ካርዲናል ሬይመንድ ቡርክ ሲሆኑ፤ የእርሳቸው አመለካከቶች በቤተሰብ እና በባዮኤቲክስ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ አቋም ያንፀባርቃል።
በተጨማሪም የ65 ዓመቱ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ፣ ከእጩዎቹ መካከል ሲሆኑ በመላው አፍሪካ እና ማዳጋስካር ኤጲስ ቆጶሳትን ይመራሉ።
እንዲሁም የ71 ዓመቱ ካርዲናል ዊለም ጃኮቡስ ኢይክ ከኔዘርላንድስ የመጡ የቀድሞ ፊዚሺያን ሌላኛው እጩ ናቸው።
ከሌሎች እጩዋች መጠነኛ የሆነ እድሎች ያሏቸው የማልታ ነዋሪ የሆኑት ካርዲናል ማሪዮ ግሬች እና ለቫቲካን የዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮ የሰሩት የፍራንሲስ የቅርብ አጋር የ69 ዓመቱ ካርዲናል ማትዮ ዙፒም ከእጮዎቹ መካከል ይገኙበታል።
የጉባኤው ጊዜ ኖቬምዲያልስ በመባል የሚታወቀውን የዘጠኝ ቀን የሀዘን ጊዜን ይከተላል። ከዚያም ካርዲናሎች በሲስቲን ቻፕል ውስጥ ለብቻቸው ይሰበሰባሉ። አዲስ ጳጳስ እስኪመረጥ ድረስም በቀን አራት ጊዜ የድምጽ መስጠት ስነ-ስርዓቱ ይካሄዳል።
አዲስ ጳጳስ በተሳካ ሁኔታ ሲመረጥም ከሲስቲን ቻፕል የጭስ ማውጫ ውስጥ ነጭ ጭስ ይለቀቃል፤ ይህም ምርጫው መጠናቀቁን እና አዲስ ጳጳስ መመረጡን ለሕዝብ ማሳወቂያ ምልክት ነው።
በሴራን ታደሰ