ሩሲያ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከዩክሬን ጋር ለመደራደር ዝግጁ ናት - ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

11 Hrs Ago 102
ሩሲያ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከዩክሬን ጋር ለመደራደር ዝግጁ ናት - ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

ሩሲያ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከዩክሬን ጋር የሰላም ድርድር ለማድረግ ዝግጁ ናት ሲሉ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ገለፁ፡፡

ፑቲን ይህን የገለፁት የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ አራተኛውን የሞስኮ ጉብኝት ካደረጉ በኋላ ነው።

ቭላድሚር ፑቲን ከስቲቭ ዊትኮፍ ጋር ባደረጉት ውይይት የሩስያ ወገን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ከዩክሬን ጋር የሚያደርገውን ድርድር ለመቀጠል ዝግጁ መሆኑን መግለፃቸውን የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

ልዩ መልዕክተኛው ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ከተወያዩ በኋላ፤ ሩሲያ እና ዩክሬን የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችል ፍሪያማ ውይይት ከሩሲያ ባለስልጠናት ጋር ማከናወናቸውን ገልፀዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከውይይቱ መጠናቀቅ በኋላ በሰጡት አስተያየትም፤ ሩሲያ እና አሜሪካ በሰላም ድርድሩ ዙሪያ ጥሩ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸው፤ ሩሲያ እና ዩክሬን ስምምነት ላይ ለመድረስ መቃረባቸውን ተናግረዋል።

አሜሪካ ባቀረበችው የተኩስ አቁም ስምምነት መሠረት ዩክሬን የተወሰኑ ግዛቶቿ በሩሲያ ሥር እንዲሆኑ እንደምትፈቅድ ፕሬዝዳንቱ አክለዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ቀብር ስነ ስርአት ቀደም ብለው በሮም ጣልያን ተገናኝተው ተነጋግረዋል፡፡

ሁለቱ መሪዎች በዩክሬን ያለውን ጦርነት ለማቆም ስምምነት ላይ ለመድረስ አመርቂ ውይይት ማካሄዳቸውን የዋይት ሀውስ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት ስቲቨን ቼንግ አመልክተዋል።

የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን፤ የአውሮፓ ህብረት ከሩሲያ ጋር ጦርነቱን ለማቆም ዩክሬን የምታደርገውን ማንኛውም ድርድር ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬን ጦር ከኩርስክ ኦብላስት መውጣቱን ካስታወቁ በኋላ ሞስኮ ከኪየቭ ጋር የሰላም ድርድር ለማድረግ ዝግጁ ናት ሲሉ ተናግረዋል።

ፑቲን ሩሲያ ኩርስክ ኦብላስትን ሙሉ ለሙሉ መቋጣጠሯን ቢገልፁም፤ ዩክሬን በኩርስክ ግዛት አሁንም ውጊያ መቀጠሉን ማስታወቋን የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡   

በንፍታሌም እንግዳወርቅ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top