ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰሞኑ የጣሉት አዲሱ ታሪፍ በመላው እስያ እና አውሮፓ የአክሲዮን ገበያ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ ማድረጉ ተገለፀ፡፡
በእስያ የአክሲዮን ገበያ ሰኞ ማለዳ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱ የተነገረ ሲሆን፤ በተለይም በጃፓን፣ በሆንክ ኮንግ፣ ቻይና፣ ታይዋን እና ደቡብ ኮሪያ የሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት ከፍተኛ የአክሲዮን ገበያ ማሽቆልቆል እንደደረሳባቸው ተገልጿል፡፡
በታሪፉ ምክንያት የጃፓኑ ኒኬኪ በ6.3 በመቶ ሲወርድ የሆንግ ኮንግ ሃንግ ሴንግ ደግሞ 9.8 በመቶ ያህል ድርሻውን ማጣቱ ተጠቅሷል።
እንዲሁም የደቡብ ኮሪያው ኮስፒ የአክሲዮን ገበያው በ5.6 በመቶ ሲቀንስ፤ በታይዋን የሚገኘው ታዬክስ ደግሞ በ9.7 በመቶ አሽቆልቁሏል ተብሏል፡፡
በኢ-ኮሜርስ ዘርፍ ግዙፍ ስም ያለው አሊባባ ግሩፕ ሆልዲንግስ በ18 በመቶ ድርሻው መቀኑሰም ተነግሯል፡፡
ከታሪፍ ውሳኔው ጋር ተያይዞ የአክሲዮን ገበያ በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰው በአውሮፓ ሲሆን፤ በተለይም በአህጉሪቱ በሚገኙ የመከላከያ ተቋማት እና ባንኮች ውስጥ ያለው የአክሲዮን ድርሻ ከፍተኛ ውድቀት ታይቶበታል ተብሏል።
በጀርመን ውስጥ ታንክ አምራች የሆነው ራይንሜትል ወደ 24 በመቶ የአክሲዮን ገበያው ዝቅ ሲል፤ የእንግሊዙ ሮልስ ሮይስ 12 በመቶ ድርሻው መቀነሱ ተነግሯል።
ከባንኮች መካከል የባርክሌይ ባንክ አክሲዮን በ 8 በመቶ ሲቀንስ፤ ናትዌስት ደግሞ 7 በመቶ ድረሻውን ማጣቱ ተመላክቷል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የተጣለው ታሪፍ በዓለም ገበያ ላይ የፈጠረውን አለመረጋጋት አስመልከቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ አንዳንድ ነገሮችን ለማስተካከል መድሃኒት መውሰድ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።
የታሪፍ መጠን ዓላማው የአሜሪካ መንግስት ገቢን በከፍተኛ ሁኔታ ለመጨመር እና ዜጎች የሀገር ውስጥ ምርቶችን በብዛት እንዲጠቀሙ በማድረግ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ለማነቃቃት ታስቦ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
በአሜሪካ ግዙፉ የሆነው ጄፒ ሞርጋን የትራምፕን የታሪፍ እርምጃ ተከትሎ የአሜሪካ እና የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ 60 በመቶ የመውደቅ እድል እንዳለው መተንበዩን ቢቢሲ ዘግቧል።